የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ባወጣው መግለጫ እ.ኤ.አ ለ2026/27 የትምህርት ዘመን ብቁ የሆኑ ኢትዮጵያውያን አመልካቾችን አወዳድሮ በሩሲያ በሚገኙ የሳይንስና የምህንድስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዲግሪ ለማስተማር ምዝገባ መጀመሩን አስታውቋል።
ይህ ተስፋ ሰጪ የትምህርት ዕድል የተመቻቸው የኢትዮጵያ እና የሩሲያ መንግስታት በኒውክሌር ልማት ፕሮጀክት ዙሪያ ካደረጉት ታሪካዊ ስምምነት እና ሀገሪቱ በዘርፉ የጀመረቻቸውን ተከታታይ የፖሊሲ እርምጃዎች ተከትሎ ነው።
ኮሚሽኑ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት የትምህርት ዕድሉ ከሚሰጥባቸው ዋና ዋና ዘርፎች የኒውክሌር ኃይል ምህንድስና ቴክኖሎጂ እና የኒውክሌር ኃይል ጣቢያዎች ዲዛይን እና የቴክኖሎጂ ሥርዓቶች ማኔጅመንት ይገኙበታል።
በዚህም ለመጀመሪያ ዲግሪ አመልካቾች ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት ያልበለጠ እና የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ አማካኝ ውጤታቸው ከ500 በላይ ሊሆን እንደሚገባ የተገለጸ ሲሆን ለሁለተኛ ዲግሪ ደግሞ ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት ያልበለጠ እና በሳይንስና ምህንድስና ዘርፍ በከፍተኛ ውጤት የተመረቁ መሆን እንዳለባቸው ተመልክቷል።
በተጨማሪም ማስታወቂያው በወጣ በ5 ተከታታይ ቀናት ውስጥ አመልካቾች ሰነዶቻቸውን በኮሚሽኑ ኢሜል መላክ እንደሚችሉ ተገልጾ ሴት አመልካቾችም እንዲበረታቱ ጥሪ ቀርቧል።
ይህ የሰው ኃይል የማፍራት ዕቅድ ወደ ተግባር የተሸጋገረው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ49ኛው መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ማቋቋሚያ ደንብን በሙሉ ድምፅ ከወሰነ በኋላ ነው።
ኮሚሽኑ የተቋቋመው ሀገሪቱ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ መንገድ በኤሌክትሪክ ኃይል፣ በኢንዱስትሪ፣ በምግብ ዋስትና፣ በጤና እና በምርምር ዘርፎች ከዓለም አቀፍ ማዕቀፎች ጋር በተጣጣመ መልኩ ጥቅም ላይ እንድታውል የመምራትና የማስተባበር ኃላፊነት ተሰጥቶት ነው።
የኮሚሽኑን መቋቋም ተከትሎ በወርሃ መስከረም በተካሄደው የዓለም የአቶሚክ ሳምንት ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በተገኙበት የኒውክሌር ልማት ፕሮጀክት የድርጊት መርሃ ግብር ስምምነት ተፈርሟል።
በወቅቱ የሮሳቶም ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሌክሲ ሊካቼቭ እና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ የተፈራረሙትን ሰነድ የተለዋወጡ ሲሆን ስምምነቱ የሩሲያን የኒውክሌር ጠበብት ከኢትዮጵያ የተማረ የሰው ኃይል ጋር በማጣመር ለአፍሪካ ተምሳሌት የሚሆን የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ለመገንባት ያለመ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቀደም ሲል ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በቀጣይ ጥቂት ዓመታት ውስጥ በ30 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ከምትጀምራቸው ስድስት ግዙፍ ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ “ለሰላማዊ ዓላማ ብቻ የሚያገለግል የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ” መሆኑን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
በዚህም አሁን የተጀመረው የተማሪዎች ስልጠናም የዚሁ ግዙፍ ሀገራዊ እቅድ የመጀመሪያው ተግባራዊ እርምጃ መሆኑ ይታወቃል።