Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ኢትዮጲያ

ተጠናክሮ የቀጠለው የኢትዮጵያ የኒውክሌር ባለቤትነት ጉዞ!

SM Samuel Mulgeta May 29, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 333 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
ተጠናክሮ የቀጠለው የኢትዮጵያ የኒውክሌር ባለቤትነት ጉዞ!

ሀገራዊ የኒውክሌር መሰረተ ልማት ለመገንባት እና በዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን በሩሲያ ስመጥር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለማስተማር የትምህርት ዕድል ጥሪ ይፋ ሁኗል።

 

የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ባወጣው መግለጫ .. 2026/27 የትምህርት ዘመን ብቁ የሆኑ ኢትዮጵያውያን አመልካቾችን አወዳድሮ በሩሲያ በሚገኙ የሳይንስና የምህንድስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዲግሪ ለማስተማር ምዝገባ መጀመሩን አስታውቋል።

 

Advertisement
Your ad could be here — contact us

ይህ ተስፋ ሰጪ የትምህርት ዕድል የተመቻቸው የኢትዮጵያ እና የሩሲያ መንግስታት በኒውክሌር ልማት ፕሮጀክት ዙሪያ ካደረጉት ታሪካዊ ስምምነት እና ሀገሪቱ በዘርፉ የጀመረቻቸውን ተከታታይ የፖሊሲ እርምጃዎች ተከትሎ ነው።

 

ኮሚሽኑ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት የትምህርት ዕድሉ ከሚሰጥባቸው ዋና ዋና ዘርፎች የኒውክሌር ኃይል ምህንድስና ቴክኖሎጂ እና የኒውክሌር ኃይል ጣቢያዎች ዲዛይን እና የቴክኖሎጂ ሥርዓቶች ማኔጅመንት ይገኙበታል።

 


በዚህም ለመጀመሪያ ዲግሪ አመልካቾች ዕድሜያቸው 20 ዓመት ያልበለጠ እና የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ አማካኝ ውጤታቸው 500 በላይ ሊሆን እንደሚገባ የተገለጸ ሲሆን ለሁለተኛ ዲግሪ ደግሞ ዕድሜያቸው 30 ዓመት ያልበለጠ እና በሳይንስና ምህንድስና ዘርፍ በከፍተኛ ውጤት የተመረቁ መሆን እንዳለባቸው ተመልክቷል።

 

በተጨማሪም ማስታወቂያው በወጣ 5 ተከታታይ ቀናት ውስጥ አመልካቾች ሰነዶቻቸውን በኮሚሽኑ ኢሜል መላክ እንደሚችሉ ተገልጾ ሴት አመልካቾችም እንዲበረታቱ ጥሪ ቀርቧል።

 

ይህ የሰው ኃይል የማፍራት ዕቅድ ወደ ተግባር የተሸጋገረው የሚኒስትሮች ምክር ቤት 49ኛው መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ማቋቋሚያ ደንብን በሙሉ ድምፅ ከወሰነ በኋላ ነው።

 

ኮሚሽኑ የተቋቋመው ሀገሪቱ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ መንገድ በኤሌክትሪክ ኃይል፣ በኢንዱስትሪ፣ በምግብ ዋስትና፣ በጤና እና በምርምር ዘርፎች ከዓለም አቀፍ ማዕቀፎች ጋር በተጣጣመ መልኩ ጥቅም ላይ እንድታውል የመምራትና የማስተባበር ኃላፊነት ተሰጥቶት ነው።

 

የኮሚሽኑን መቋቋም ተከትሎ በወርሃ መስከረም በተካሄደው የዓለም የአቶሚክ ሳምንት ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በተገኙበት የኒውክሌር ልማት ፕሮጀክት የድርጊት መርሃ ግብር ስምምነት ተፈርሟል።

 

በወቅቱ የሮሳቶም ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሌክሲ ሊካቼቭ እና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ የተፈራረሙትን ሰነድ የተለዋወጡ ሲሆን ስምምነቱ የሩሲያን የኒውክሌር ጠበብት ከኢትዮጵያ የተማረ የሰው ኃይል ጋር በማጣመር ለአፍሪካ ተምሳሌት የሚሆን የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ለመገንባት ያለመ ነበር።

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቀደም ሲል ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በቀጣይ ጥቂት ዓመታት ውስጥ 30 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ከምትጀምራቸው ስድስት ግዙፍ ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱለሰላማዊ ዓላማ ብቻ የሚያገለግል የኒውክሌር ኃይል ማመንጫመሆኑን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

 

በዚህም አሁን የተጀመረው የተማሪዎች ስልጠናም የዚሁ ግዙፍ ሀገራዊ እቅድ የመጀመሪያው ተግባራዊ እርምጃ መሆኑ ይታወቃል።

 

SM
ስለ ጸሐፊው

Samuel Mulgeta

29 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።