Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

መንግሥት በታክስ ላይ ያወጣው አዲሱ መመሪያ ምን ይላል?

SM Samuel Mulgeta May 25, 2026 Updated 3h ago 3 ደቂቃ ንባብ 409 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
መንግሥት በታክስ ላይ ያወጣው አዲሱ መመሪያ ምን ይላል?

የታክስ ተመላሽ ክፍያ በሕጉ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሳይፈጸም ቢዘገይ፣ የገቢዎች ሚኒስቴር ለታክስ ከፋዩ መመለስ ያለበትን ገንዘብ ከወለድ ጋር እንዲከፍል የሚያስገድድ አዲስ መመሪያ ወጥቷል።

 

የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ተመላሽ አሰጣጥ ሥርዓትን ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መልኩ ለመምራት ያስችላል ያለውን "የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመላሽ የሚደረግበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣ መመሪያ ቁጥር 1132/2018" አውጥቷል።

 

Advertisement
Your ad could be here — contact us

ይህ አዲስ መመሪያ የወጣው ቀደም ሲል የነበረው የታክስ አዋጅ ተሽሮ በአዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 1341/2016 መተካቱን ተከትሎ ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም የታክስ ተመላሽ አገልግሎትን የታክስ ከፋዮችን የስጋት ደረጃ መሠረት ባደረገ መልኩ ዘመናዊ ለማድረግ ነው።

 

መመሪያው የታክስ ተመላሽ ጥያቄ የሚያቀርቡ ከፋዮችን በሦስት ዋና ዋና የስጋት ደረጃዎች የሚከፍል ሲሆን፣ ይህም የኦዲትና የማጣራት ሥራው በታማኝ ከፋዮች ላይ የሚፈጥረውን እንግልት ለመቀነስ ያለመ ነው ይላል።

 

በዚህም መሠረት ዝቅተኛ የስጋት ደረጃ ያላቸው ከፋዮች ሰፊ ኦዲት ሳይደረግባቸው በተፋጠነ ሁኔታ ተመላሽ የሚያገኙበት ሥርዓት ሲዘረጋ፣ መካከለኛና ከፍተኛ የስጋት ደረጃ ላይ የሚገኙ ከፋዮች ደግሞ እንደሁኔታው ዝርዝርና ጥብቅ የሰነድ ማጣራት እንዲሁም የኦዲት ምርመራ ይደረግባቸዋል።

 

ይህም በመንግሥት ገቢ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመከላከልና ተገቢው የታክስ ተመላሽ ለትክክለኛው ከፋይ መድረሱን ለማረጋገጥ ይረዳል ይላል።

 

በመመሪያው ዝርዝር አፈጻጸም መሠረት፣ በዜሮ የማስከፈያ ልክ ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ለሚልኩ አምራቾች፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወርቅ ለሚያቀርቡና 100 ሚሊዮን ብር በላይ የካፒታል ዕቃ ግዥ ለፈጸሙ ከፋዮች ልዩ ትኩረት ሰጥቷል።

 

በተለይም በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተመርጠው ወደ ውጭ ላኪነት የተሰማሩ አምራቾች ምርታቸውን ወደ ውጭ ከመላካቸው በፊት በሀገር ውስጥ ለገዟቸው ግብዓቶች የከፈሉት ታክስ በሰባት ቀናት ውስጥ የሚመለስበት "የተፋጠነ የተመላሽ ሥርዓት" ተዘርግቷል።

 

ሌሎች መደበኛ የተመላሽ ጥያቄዎች ደግሞ አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎባቸው በአርባ አምስት ቀናት ውስጥ ውሳኔ እንዲያገኙ በመመሪያው ተደንግጓል።

 

የታክስ ተመላሽ ጥያቄ የሚያቀርቡ አካላት ሊያሟሏቸው የሚገቡ ጥብቅ ቅድመ ሁኔታዎችም በመመሪያው የተካተቱ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ግብይቱ የተፈጸመባቸው ሕጋዊ ኦርጅናል ደረሰኞች፣ የባንክ ክፍያ ማረጋገጫዎችና ሌሎች ተያያዥ ሰነዶች ይገኙበታል።

 

መመሪያው በተለየ ሁኔታ ካስቀመጣቸው ነጥቦች መካከል፣ ከሐምሌ 1 ቀን 2017 . ጀምሮ 50,000 (ሃምሳ ሺህ) ብር በላይ የሆኑ ማናቸውም ግብይቶች በባንክ በኩል ካልተፈጸሙና የጥሬ ገንዘብ ግብይት ገደብን ካላለፉ ለታክስ ተመላሽ ጥያቄ ተቀባይነት እንደማይኖራቸው በግልጽ አስፍሯል።

 

የታክስ ባለሥልጣኑ (ገቢዎች ሚኒስቴር) ተመላሽ ሊደረግ የሚገባውን ገንዘብ በሕጉ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሳይከፍል ከዘገየ፣ ለከፋዩ የወለድ ክፍያ የመክፈል ግዴታ የሚኖርበት መሆኑን መመሪያው ያዛል።

 

ወለዱ የተመላሸ ሒሣብ መከፈል ከነበረበት አግባብነት ካለው ጊዜ መጨረሻ ጀምሮ ተመላሹ ሒሣብ እስከተከፈለ ድረስ ላለው ጊዜ የሚሰላ ሲሆን የወለድ ምጣኔውም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ባንኮች የንግድ ብድር የሚሰጡበት ከፍተኛው የወለድ ምጣኔ መሰረት ይሆናል፡፡

 

ወለዱን ለመክፈል አግባብ ላለው ፍርድ ቤት ቀርቦ የተሰጠ ውሳኔ ማስረጃ በማያያዝ ውሳኔው በተሰጠበት 6 ወራት ጊዜ ውስጥ መቅረብ አለበት፤ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ያልቀረበ ጥያቄ መብቱ እንደተወ እንደሚቆጠርም መመሪያው ደንግጓል፡፡

 

 

 

SM
ስለ ጸሐፊው

Samuel Mulgeta

27 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።