የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ተመላሽ አሰጣጥ ሥርዓትን ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መልኩ ለመምራት ያስችላል ያለውን "የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመላሽ የሚደረግበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣ መመሪያ ቁጥር 1132/2018" አውጥቷል።
ይህ አዲስ መመሪያ የወጣው ቀደም ሲል የነበረው የታክስ አዋጅ ተሽሮ በአዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 1341/2016 መተካቱን ተከትሎ ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም የታክስ ተመላሽ አገልግሎትን የታክስ ከፋዮችን የስጋት ደረጃ መሠረት ባደረገ መልኩ ዘመናዊ ለማድረግ ነው።
መመሪያው የታክስ ተመላሽ ጥያቄ የሚያቀርቡ ከፋዮችን በሦስት ዋና ዋና የስጋት ደረጃዎች የሚከፍል ሲሆን፣ ይህም የኦዲትና የማጣራት ሥራው በታማኝ ከፋዮች ላይ የሚፈጥረውን እንግልት ለመቀነስ ያለመ ነው ይላል።
በዚህም መሠረት ዝቅተኛ የስጋት ደረጃ ያላቸው ከፋዮች ሰፊ ኦዲት ሳይደረግባቸው በተፋጠነ ሁኔታ ተመላሽ የሚያገኙበት ሥርዓት ሲዘረጋ፣ መካከለኛና ከፍተኛ የስጋት ደረጃ ላይ የሚገኙ ከፋዮች ደግሞ እንደሁኔታው ዝርዝርና ጥብቅ የሰነድ ማጣራት እንዲሁም የኦዲት ምርመራ ይደረግባቸዋል።
ይህም በመንግሥት ገቢ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመከላከልና ተገቢው የታክስ ተመላሽ ለትክክለኛው ከፋይ መድረሱን ለማረጋገጥ ይረዳል ይላል።
በመመሪያው ዝርዝር አፈጻጸም መሠረት፣ በዜሮ የማስከፈያ ልክ ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ለሚልኩ አምራቾች፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወርቅ ለሚያቀርቡና ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የካፒታል ዕቃ ግዥ ለፈጸሙ ከፋዮች ልዩ ትኩረት ሰጥቷል።
በተለይም በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተመርጠው ወደ ውጭ ላኪነት የተሰማሩ አምራቾች ምርታቸውን ወደ ውጭ ከመላካቸው በፊት በሀገር ውስጥ ለገዟቸው ግብዓቶች የከፈሉት ታክስ በሰባት ቀናት ውስጥ የሚመለስበት "የተፋጠነ የተመላሽ ሥርዓት" ተዘርግቷል።
ሌሎች መደበኛ የተመላሽ ጥያቄዎች ደግሞ አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎባቸው በአርባ አምስት ቀናት ውስጥ ውሳኔ እንዲያገኙ በመመሪያው ተደንግጓል።
የታክስ ተመላሽ ጥያቄ የሚያቀርቡ አካላት ሊያሟሏቸው የሚገቡ ጥብቅ ቅድመ ሁኔታዎችም በመመሪያው የተካተቱ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ግብይቱ የተፈጸመባቸው ሕጋዊ ኦርጅናል ደረሰኞች፣ የባንክ ክፍያ ማረጋገጫዎችና ሌሎች ተያያዥ ሰነዶች ይገኙበታል።
መመሪያው በተለየ ሁኔታ ካስቀመጣቸው ነጥቦች መካከል፣ ከሐምሌ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ከ50,000 (ሃምሳ ሺህ) ብር በላይ የሆኑ ማናቸውም ግብይቶች በባንክ በኩል ካልተፈጸሙና የጥሬ ገንዘብ ግብይት ገደብን ካላለፉ ለታክስ ተመላሽ ጥያቄ ተቀባይነት እንደማይኖራቸው በግልጽ አስፍሯል።
የታክስ ባለሥልጣኑ (ገቢዎች ሚኒስቴር) ተመላሽ ሊደረግ የሚገባውን ገንዘብ በሕጉ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሳይከፍል ከዘገየ፣ ለከፋዩ የወለድ ክፍያ የመክፈል ግዴታ የሚኖርበት መሆኑን መመሪያው ያዛል።
ወለዱ የተመላሸ ሒሣብ መከፈል ከነበረበት አግባብነት ካለው ጊዜ መጨረሻ ጀምሮ ተመላሹ ሒሣብ እስከተከፈለ ድረስ ላለው ጊዜ የሚሰላ ሲሆን የወለድ ምጣኔውም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ባንኮች የንግድ ብድር የሚሰጡበት ከፍተኛው የወለድ ምጣኔ መሰረት ይሆናል፡፡
ወለዱን ለመክፈል አግባብ ላለው ፍርድ ቤት ቀርቦ የተሰጠ ውሳኔ ማስረጃ በማያያዝ ውሳኔው በተሰጠበት በ6 ወራት ጊዜ ውስጥ መቅረብ አለበት፤ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ያልቀረበ ጥያቄ መብቱ እንደተወ እንደሚቆጠርም መመሪያው ደንግጓል፡፡