የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት የባሕር በር ፍላጎት አጀንዳውን አጠናክሮ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ግብፅ ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር የምታደርገውን ጥረት ለማደናቀፍ የምታደርገውን እንቅስቃሴ አጠናክራ መቀጠሏን ይፋ አድርጓል።
ይህም ማለት በተለይ ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄዋን በይፋ ማቅረቧን ተከትሎ ግብፅ ጉዳዩን ለማፈን በቀጠናው ላይ “ከበባ በሚመስል መልኩ” ውጥረትና ትንኮሳዎችን የመፍጠር አዝማሚያዋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሯን የሚያሳይ ነው።
በእርግጥ ይህ ስልት አዲስ ሳይሆን ግብፅ ለዘመናት ስትከተለው የቆየችው የቆየ ስትራቴጂ መሆኑን የገለጹት የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ኢትዮጵያን ለማነቅ የሚደረጉ መሰናክሎች ቢበራከቱም የኢትዮጵያ መንግሥት ግን የባሕር በር አጀንዳውን ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ አሁን ላይ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መንግሥታትና ተቋማት ዘንድ ተቀባይነትና ድጋፍ እያገኘ የመጣ እንዲሁም የአገሪቱ ሕዝብ በሙሉ የደገፈው አጀንዳ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፤ መንግሥት ይህንን ፖሊሲና ፍላጎት ለማሳካት የሚከተለው መንገድ ሙሉ በሙሉ ሰላማዊ፣ ሕጋዊና ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ ብቻ መሆኑን ለተለያዩ ሀገራት መሪዎች አበክሮ ማስረዳቱ ተገልጿል፡
ለዚህም ማሳያ የሚሆነው የተለያዩ የዓለም ሀገራት መሪዎች፣ አምባሳደሮችና ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ እንግዶች ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የባሕር በር ፍላጎት ፍትሐዊነት በመገንዘብ ጥያቄው በድርድርና በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ ያላቸውን ጽኑ ድጋፍ በተለያየ ጊዜ መግለጻቸው ነው።
እነዚህ ዓለም አቀፍ አካላት ኢትዮጵያ የምታደርገውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በበጎ በመመልከት ለቀጠናው ዘላቂ ልማትና የጋራ እድገት ሲባል ጉዳዩ በሰላማዊ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ላይ ተመስርቶ መፈታት እንዳለበት በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ በግብፅ እና በኤርትራ በኩል የተሰጡ ይፋዊ መግለጫዎች እንደሚያሳዩት ካይሮ ከአሥመራ ጋር ያላትን ወታደራዊና ስትራቴጂካዊ ትስስር በማጥበቅ የኢትዮጵያን ቀጠናዊ ግስጋሴ ለመግታት ግልጽ የሆነ ምላሽ መስጠት ጀምራለች።
በዚሁ መሠረት ሁለቱ ሀገራት በአሥመራ ባደረጉት ከፍተኛ የውይይት መድረክ ላይ የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ውድቅ ለማድረግ የሚመስሉ ሦስት ዋና ዋና መመዘኛዎችንና አቋሞችን አስቀምጠዋል።

የመጀመሪያው የቀይ ባሕር አስተዳደር እና የደኅንነት ጉዳይ በጥብቅ የሚመለከተው የቀይ ባሕር ጠረፍ አገራትን ብቻ እንደሆነና ከአካባቢው ውጭ ያሉ ሌሎች አካላት በጉዳዩ ላይ ጣልቃ መግባት እንደሌለባቸው ማስጠንቀቃቸው ሲሆን በቀይ ባሕር ዙሪያ የሚነሱ ጉዳዮች ከቀይ ባሕር ዳርቻ ሀገራት ብሔራዊ ደኅንነት ጋር ቀጥተኛ ትስስር ያላቸው በመሆኑ አጎራባች ያልሆነ ማንኛውም አካል በጉዳዩ ላይ እጁን ማስገባት የለበትም የሚል አቋም መያዛቸው ሌላኛው ነው።
በተጨማሪም ግብፅ ኤርትራ ቀይ ባሕርን በማስተዳደር ረገድ ያላትን ዓላማ ሙሉ በሙሉ እንደምትደግፍ ለቀይ ባሕር አጎራባች ሀገራት አንድነትና ሉዓላዊነት ዕውቅና እንደምትሰጥ በይፋ አረጋግጣለች።
እነዚህ ሦስት ስምምነቶች ተጠናክረው ሁለቱ ሀገራት በቀይ ባሕር ላይ የሚደረገውን የካርጎ እንቅስቃሴ እና የወደብ ትስስር የሚያጠናክር አዲስ የባሕር ትራንስፖርት ስምምነት ተፈራርመዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ግብፅና ኤርትራ በአሥመራና በካይሮ ወደቦች መካከል አዲስ የቀጥታ የመርከብ መስመር ለመዘርጋት መወሰናቸውም ተሰምቷል፡፡
ይህ ማለት ኤርትራ እና የታችኛው የተፋሰስ ሀገር የሆነችው ግብፅ ወታደራዊና የንግድ ትስስራቸውን በእጥፍ ማሳደጋቸው ብቻ ሳይሆን የቀይ ባሕርን የጸጥታ ይዞታ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ መዋቅራዊ ጥረት መጀመራቸውን ያሳያል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎቷን በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማሳካት ዓለም አቀፍ ድጋፍ እያገኘች ባለችበት በአሁኑ ወቅት፣ ግብፅና ኤርትራ ይህንን ጥረት ለማደናቀፍና ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር ለማራቅ ወታደራዊና የንግድ ትስስራቸውን በማጥበቅ ቀጠናዊ ከበባ ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት የተደቀኑበትን መሰናክሎች ሁሉ በመቋቋም የባሕር በር አጀንዳውን ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በቁርጠኝነት አስታውቋል።