Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
አስተያየት

ተሳፋሪ እና አሽከርካሪዎችን ወደ ግጭት እያመራ የሚገኘው የታሪፍ ጭማሪ

A Administrator May 20, 2026 Updated 3h ago 3 ደቂቃ ንባብ 402 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
ተሳፋሪ እና አሽከርካሪዎችን ወደ ግጭት እያመራ የሚገኘው የታሪፍ ጭማሪ

በአዲስ አበባ ከተማ በትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪ ምክንያት አሽከርካሪዎች እንዲሁም ረዳቶች ከተሳፋሪ ጋር ሲጨቃጨቁ ብሎም ወደ ጸብ ሲያመሩ ማየት የተለመደ ነው።


በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ከተቀሰሰ ወዲህ ባጋጠመው ዓለም አቀፍ የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎል ሳቢያ በነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ተደጋጋሚ የዋጋ ማስተካከያ መደረጉን ተከትሎ የትራንስፖርት ዘርፉን ክፉኛ እየረበሸው ይገኛል፡፡ 


ይህ ማሻሻያ ከመጋቢት 7/2018 ዓ.ም ጀምሮ የተደረገ ቢሆንም የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የዓለም የነዳጅ ዋጋን መሰረት በማድረግ ከሚያዚያ 23 ቀን 2018 ጀምሮ የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ላደረገው ጭማሪ ግን ይፋዊ የታሪፍ ማሻሻያ አለመደረጉ ይታወቃል።

Advertisement
Your ad could be here — contact us


ይሁን እንጂ በመዲናዋ የተለያየ አካባቢ የሚጓጓዝ የከተማዋ ነዋሪ በመውጫ ሰአቱ፣ በመግቢያ ሰአቱ ብሎም በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ለሁለተኛ ዙር በተደረገው የነዳጅ ጭማሪ ምክንያት ዋጋ ጨምረናል ከሚሉ የታክሲ አሽከርካሪዎች ጋር መብቱን ለማስከበር እየተከራከረ ይታያል። 

photo_2026-05-20_14-54-00


ይህንንም የሰማው የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ምንም ዓይነት የታሪፍ ማሻሻያ ሳይደረግ በዘፈቀደ ዋጋ የሚጨምሩ አሽከርካሪዎችና ባለንብረቶች ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስታወቋል።


በዚህም እስካሁን ድረስ ከቢሮው የተላለፈ የትራንስፖርት ታሪፍ ማሻሻያ ለማድረግ የሚያስችል ምንም ዓይነት ውሳኔ የሌለ ሲሆን በየትኛውም የትራንስፖርት መስመር ከቢሮው ዕውቅና ውጪ የሚደረግ የዋጋ ጭማሪ ሕገ-ወጥ መሆኑ ተገልጿል። 

 

እንዲሁም ቀደም ሲል የተደረገው የታሪፍ ማሻሻያ ወደፊት ሊደረግ የሚችለውን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ታሳቢ ያደረገ መሆኑ የተጠቆመ ቢሆንም ከአሽከርካሪዎች ግን ይሁንታን ያገኘ አይመስልም። 


በተጨማሪም ቢሮው ወቅታዊውን ሁኔታ መሠረት በማድረግ አስፈላጊውን ጥናት እያከናወነ ቢሆንም ጥናቱ ተጠናቆ ይፋዊ መመሪያ እስካልወጣ ድረስ ነባሩ ታሪፍ ተፈጻሚ መሆን እንዳለበት አሳስቦ ነበር።


በሕገ-ወጥ መንገድ የታሪፍ ጭማሪ በሚያደርጉና ተሳፋሪዎችን በሚያጉላሉ አካላት ላይ ቢሮው የቁጥጥር ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም የተገለጸ ሲሆን በዚህ የሕግ ጥሰት ውስጥ የሚሳተፉ አሽከርካሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የትራንስፖርት ማኅበራትና ባለንብረቶችም ጭምር አስተማሪ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶ ቆይቷል።


ነገር ግን አሁንም ቢሆን በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች የሚገኙ አሽከርካሪዎች ከመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት በኋላ የነዳጅ ዋጋ ለሁለተኛ ጊዜ ሲጨምር የትራንስፖርት ታሪፍም ተጨምሯል በሚል በእድሜያቸው ከፍ ካሉ እንዲሁም ህግ ይከበር ከሚሉ ወጣቶች ጋር ያለውን ግብግብ የገበያ ሚዲያ ሪፖርተር በተለያየ ቦታ ሲዘዋወር መታዘብ ችሏል። 


ይሁን እንጂ ተሳፋሪዎች ከሕጋዊው ታሪፍ ውጪ ተጨማሪ ክፍያ የሚጠይቁ አሽከርካሪዎች ሲያጋጥሟቸው በቢሮው ነፃ የስልክ መስመር 9417 ላይ በመደወል ጥቆማ እንዲሰጡ ጥሪ ሲቀርብ የቆየ ሲሆን የቁጥጥር ሂደቱ እንግልቱን፣ ክርክሩን ብሎም የተሳፋሪውን መብት አስከብሯል ለማለት ያስቸግራል።


በዚህም ጥቆማ በተሰጠበት ወቅት በአቅራቢያው ያሉ የትራፊክ ፖሊሶች ወይም የቢሮው ተቆጣጣሪዎች በቦታው ፈጥነው በመገኘት በሕግ ጥሰት ላይ የተሰማሩ አሽከርካሪዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ የሚወስዱበት የቅንጅት አሠራር ሊጠናከር ይገባል።


በተጨማሪም ቁጥጥሩ በአሽከርካሪዎች ላይ ብቻ ከማተኮር ወጥቶ የትራንስፖርት ማኅበራትንና ባለንብረቶችን ቢያካትት ማኅበራት አባሎቻቸው የሆኑት አሽከርካሪዎች ሕጋዊውን አሠራር እንዲከተሉ የማድረግና የስነ-ምግባር ቁጥጥር የማድረግ የጋራ ኃላፊነት ስላለባቸው ጥሰት በሚፈጽሙ አሽከርካሪዎች ልክ ማኅበራቱም ላይ አስተዳደራዊ ቅጣት መጣል ቢጀመር የቁጥጥር ሥራውን ውጤታማ እንደሚያደርገው ይታመናል፡፡

A
ስለ ጸሐፊው

Administrator

12 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።