Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
አስተያየት

የሁለት አመቱ የአከራይ ተከራይ ውል ሊያበቃ ሲል የታየው የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ

SM Samuel Mulgeta May 18, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 322 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
የሁለት አመቱ የአከራይ ተከራይ ውል ሊያበቃ ሲል የታየው የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ

ከተማ አስተዳደሩ እያዘጋጀሁት ነው ያለው አዲስ ጥናት ምን መምሰል አለበት?

በሳሙኤል ሙሉጌታ

 

ከዛሬ ሁለት አመት በፊት ወደ ስራ የገባው የአከራይ ተከራይ ውል ሊያበቃ ከሁለት ወር ያነሰ ጊዜ ቀርቶታል፡፡ ይህ ለሁለት አመት ስራ ላይ የነበረውና ጭማሪን የሚከለክለው ህግ ማብቂያው ጊዜ መቃረቡን ተከትሎ አከራዮች ከ50 እስከ 100 ፐርሰንት የሚደርስ ጭማሪ እያደረጉ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ሸማቾች ተቆርቋሪ ድርጅት አስታውቋል፡፡ ለዚህ የዋጋ ጭማሪ ደግሞ እንደ ዋነኛ ምክንያት እየተጠቀሱ ያሉት በአገሪቱ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የናረው አጠቃላይ የኑሮ ውድነት እና የመሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋ መጨመር ሲሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ ከመንግስት በኩል በአከራዮች ላይ የተጣለው የታክስ ግብር መጠን አከራዮች ወጪያቸውን ሙሉ በሙሉ ወደ ተከራዩ ላይ እንዲያስተላልፉ አስገድዷቸዋል፡፡

Advertisement
Your ad could be here — contact us

 

 

 

ታዲያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቀደም ሲል አውጥቶት የነበረው የሁለት ዓመት የቤት ኪራይ ውል ቁጥጥር ማዕቀፍ በመጪው ሰኔ 30 ቀን 2018 . ሙሉ በሙሉ ያበቃል። በዚህም ይህንን የጊዜ ገደብ ማብቂያ ተከትሎ በገበያው ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ድንገተኛ መረባበሽ ለመግታት፣ አስተዳደሩ በአሁኑ ወቅት ሰፊ ጥናት እያስጠና መሆኑንና በጥናቱ ማጠቃለያ መሰረትም በቅርቡ አዲስ ውሳኔ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል። በአስተዳደሩ በኩል ፍንጭ የተሰጠው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ አዲሱ የሚወጣው ውሳኔ የቤት ኪራይ ዋጋው አሁን ባለበት እንዲቀጥል ሊያደርግ ይችላል፤ ካልሆነም ደግሞ ወቅታዊውን የገበያ ሁኔታና የአከራዮችንም ጫና ያማከለ መጠነኛና አነስተኛ ጭማሪ ብቻ ሊፈቀድ እንደሚችል ተገልል፡፡

 

ቢሆንም ግን፣ የወረቀት ላይ ህግ ብቻውን ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ እንደማይችል ካለፉት ሁለት ዓመታት የአፈጻጸም ተሞክሮ በሚገባ መማር ያስፈልጋል። ቀድሞ የነበረው ህግ በአዋጅ ደረጃ መልካም ቢሆንም፣ በመሬት ላይ ግን ህጉን በአግባቡ የሚያስፈጽም ጠንካራ መዋቅርና ተቆጣጣሪ አካል ስላልነበረው፣ አከራዮች ከመንግስት እውቅና ውጪ በድብቅ ዋጋ እንዲጨምሩ በር ከፍቶ ቆይቷል። ይህ ብቻ ሳይሆን "እራሳችን ልንገባበት ስለሆነ ቤቱን በአስቸኳይ ልቀቁ" በሚል የተዘዋዋሪ የማስፈራሪያ መንገድ ተከራዮችን ያላግባብ እንዲያፈናቅሉ እና የፈለጉትን የተጋነነ ዋጋ እንዲጭኑ ትልቅ ክፍተት ፈጥሯል። ስለዚህ በመጪው ሰኔ ወር ላይ ይፋ የሚደረገው ቀጣዩ የህግ ማዕቀፍ እነዚህን የአፈጻጸም ክፍተቶች ሙሉ በሙሉ የሚደፍንና የተከራዩን መብት የሚያስከብር መሆን ይኖርበታል።

 

ለመሆኑ አዲሱ የህግ ማዕቀፍ ምን መምሰል አለበት?

 

በመጀመሪያ ደረጃ፣ አዲሱ ህግ አከራዮች በየዓመቱ ሊያደርጉ የሚችሉትን የጭማሪ መጠን በአገሪቱ አጠቃላይ የደሞዝ እድገትና ከነባራዊው የገበያ ሁኔታ ጋር የተመጣጠነ ሆኖ፣ ከተወሰነ አነስተኛ የፐርሰንት መጠን እንዳይበልጥ በግልጽ በፐርሰንት ያስቀመጠ "የዋጋ ጣሪያ" ሊኖረው ይገባል። ይህም አከራይም ሆነ ተከራይ የወደፊት እጣ ፈንታቸውን ቀድመው አውቀው እንዲረጋጉ ይረዳቸዋል።

 

በሁለተኛ ደረጃ፣ አከራዮች የተጣለባቸውን የታክስ ግብር ሰበብ በማድረግ ወጪውን ሙሉ በሙሉ ወደ ተከራዩ ማህበረሰብ እንዳያስተላልፉና የዋጋ ንረቱን እንዳያባብሱት፣ ለአከራዮች የሚሆን የተለየ የታክስ ማቃለያ ወይም የማበረታቻ ሥርዓት መዘርጋት አለበት።

 

የችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ግን መንግስት የጀመራቸውን የቤት ግንባታ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ማጠናቀቅና የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን በከፍተኛ ሁኔታ ማቃለል ነው፡፡

 

 

 

SM
ስለ ጸሐፊው

Samuel Mulgeta

27 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።