ሰሜን ኮሪያ “ኪም ከተገደሉ አውቶማቲክ የኒውክሌር ጥቃት ይሰነዘራል” የሚል ሕግ አጸደቀች
ግንቦት 01/2018 (ገበያ ሚዲያ) ሰሜን ኮሪያ የሀገሪቱ የበላይ መሪ ኪም ጆንግ ኡን በባዕድ ሀገር ኃይሎች ከተገደሉ ወይም ለስራ ብቁ ካልሆኑ፤ የሀገሪቱ ጦር ወዲያውኑ እና በራሱ ጊዜ የሚሰነዘር የኒውክሌር አጸፋዊ ጥቃት እንዲፈጽም የሚያዝ ሕገ-መንግስታዊ ማሻሻያ ማድረጓ ተሰምቷል።
ይህ አስገራሚ የተባለው የሕግ ማሻሻያ የተደረገው፤ የአሜሪካና የእስራኤል ጥምረት በኢራን ላይ በወሰዱት እርምጃ የሀገሪቱ የበላይ መሪ አያቶላ አሊ ኻሜኒ እና የቅርብ አማካሪዎቻቸው መገደላቸውን ተከትሎ ፒዮንግያንግ በገባችበት ከፍተኛ ስጋት መሆኑ ተገልጿል።
የደቡብ ኮሪያ ብሔራዊ የስለላ ተቋም (NIS) ለከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በሰጠው መግለጫ እንዳመላከተው፤ በሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ፖሊሲ ሕግ አንቀጽ 3 ላይ ማሻሻያ ተደርጓል።
ማሻሻያው “የሀገሪቱ የኒውክሌር ኃይሎች የዕዝ እና ቁጥጥር ስርዓት በጠላት ኃይሎች ጥቃት አደጋ ላይ ከወደቀ የኒውክሌር ጥቃት በራስ-ሰር እና በአፋጣኝ ይሰነዘራል” የሚል ሲሆን ይህም ማለት መሪው ኪም ጆንግ ኡን በህይወት ባይኖሩ እንኳ ጥቃቱ እንዳይቆም የሚያደርግ ስርዓት ነው።
ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር አጠቃቀም ሕጓን ስታሻሽል ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም፤ ነገር ግን የአሁኑ “አውቶማቲክ” መባሉ ለየት ያደርገዋል።
ሃገሪቷ እ.ኤ.አ በ2022 ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ባለቤትነቷ “የማይመለስ” መሆኑን የሚያውጅ ሕግ አውጥታ የነበረች ሲሆን አዲሱ ማሻሻያ ግን የኒውክሌር ትዕዛዝ ሰንሰለቱን ከመሪው ግላዊ ውሳኔ አውጥቶ ወደ “ኮምፒውተራይዝድ” ወይም ቀድሞ ወደ ተወሰነ ወታደራዊ መመሪያ ቀይሮታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሁኑን የህግ ማሻሻያ ተከትሎ በሴኡል በሚገኘው ኩክሚን ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ፕሮፌሰር የሆኑት አንድሬ ላንኮቭ የኢራን መሪዎች መገደል ለሰሜን ኮሪያ ትልቅ የማንቂያ ደወል ሆኗል ብለዋል።
አያይዘውም አሜሪካና እስራኤል የኢራንን አመራር በአጭር ጊዜ ውስጥ የመምታት ብቃታቸውን ማሳየታቸው ኪም ጆንግ ኡንን በከፍተኛ ሁኔታ እንዳስፈራቸው ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል።
ሰሜን ኮሪያ ከመሪዋ ደህንነት በተጨማሪ በደቡባዊ ድንበሯ ላይ አዲስ ዓይነት የጦር መሳሪያዎችን ለማሰማራት ማቀዷን የሀገሪቱ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ኪም ጆንግ ኡን በዚህ ሳምንት የጥይትና አረር ፋብሪካን የጎበኙ ሲሆን አዲስ የተመረተውን ባለ 155 ሚሊ ሜትር ተንቀሳቃሽ መድፍ መርምረዋል።
ይህ አዲስ መድፍ ከ60 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት የመምታት አቅም ያለው ሲሆን፤ የደቡብ ኮሪያን ዋና ከተማ ሴኡልን በቀጥታ ኢላማ ውስጥ የሚያስገባ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን መድፉ በዚህ ዓመት በድንበር አካባቢ በሚገኙ የጦር ክፍሎች ውስጥ እንደሚሰማራ ተነግሯል።
ምንም እንኳ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ስኬታማ ጥቃት ቢሰነዝሩም፤ በሰሜን ኮሪያ ላይ ተመሳሳይ እርምጃ መውሰድ አስቸጋሪ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ለዚህም ምክንያቱ የሰሜን ኮሪያ ድንበር እጅግ ጥብቅ መሆኑ የውጭ ዜጎች እንቅስቃሴ ቁጥጥር የሚደረግበት መሆኑና ሃገሪቷ እንደ ኢራን በቴክኖሎጂ (በካሜራዎች) በቀላሉ የማይሰለል አሰራር ስላላት ነው።
ኪም ጆንግ ኡን ለደህንነታቸው በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚሰጉ የሚታወቅ ሲሆን በጉዞዎቻቸው ወቅት የታጠቁ የጥበቃ አባላት እንደማይለዩአቸውና በአብዛኛው በከፍተኛ ሁኔታ በታጠቁ ባቡሮች እንደሚንቀሳቀሱ ይታወቃል።