Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

ፍርድ ቤት በካሙዙ ካሳ እና በሻኩራ ፕሮዳክሽን ላይ የእግድ ትዕዛዝ አስተላለፈ

A Administrator May 14, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 38 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
ፍርድ ቤት በካሙዙ ካሳ እና በሻኩራ ፕሮዳክሽን ላይ የእግድ ትዕዛዝ አስተላለፈ

ግንቦት 01/2018 (ገበያ ሚዲያ) በብሪክስ (BRICS) ሀገራት በተካሄደው የ”ኪነ ኢትዮጵያ” የባህል ጉብኝት ላይ የተሳተፉ 37 አርቲስቶች ያልተከፈላቸውን ከ30.8 ሚሊዮን ብር በላይ የሙያ ክፍያ ለማስመለስ በሙዚቃ አቀናባሪ ካሙዙ ካሳ እና በሻኩራ ፕሮዳክሽን ላይ ክስ መስርተዋል።

አርቲስቶቹ በሩሲያ፣ በቻይና እና በሌሎች የብሪክስ ሀገራት እንዲሁም በሀገር ውስጥ 11 ያህል የባህል ትዕይንቶችን ቢያቀርቡም በውላቸው መሰረት ሊከፈላቸው የሚገባው ክፍያ እንዳልተፈጸመላቸው ገልጸዋል።

በእያንዳንዱ አርቲስት እና በሻኩራ ፕሮዳክሽን መካከል በተደረገው ስምምነት መሰረት በአራት መድረክ ትዕይንቶች 217,500 ብር ሊከፈል ስምምነት ተደርጎ እንደነበር ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቧል።

Advertisement
Your ad could be here — contact us

ይሁን እንጂ አርቲስቶቹ ለአንድ ዓመት ከሁለት ወራት ያህል በትዕግስት ቢጠባበቁም ክፍያውን ማግኘት ባለመቻላቸው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰዳቸው ተገልጿል።

በዚህም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች በካሙዙ ካሳ እና በሻኩራ ፕሮዳክሽን የባንክ ሂሳቦች ላይ ለ20 ቀናት የሚቆይ የእግድ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

ይህም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ እንደ አቢሲኒያ፣ አዋሽ እና የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ያሉ የግል ባንኮችን የሚመለከት ሲሆን ከሂሳብ እንቅስቃሴ በተጨማሪ በካሙዙ ካሳ ንብረቶች ላይም እግድ ተጥሏል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ለጉብኝቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር በጀት መመደቡን ቀደም ሲል አስታውቆ የነበረ ሲሆን ሚኒስቴሩ ለፕሮዳክሽን ድርጅቱ በጻፈው ደብዳቤ በጀቱ ለሻኩራ እና ለካሙዙ መለቀቁን አረጋግጦ ድርጅቱ ለአርቲስቶቹ ክፍያ እንዲፈጽም አሳስቧል።

ይሁን እንጂ ሚኒስቴሩ ውል የገባው በቀጥታ ከአርቲስቶቹ ጋር ሳይሆን ከሻኩራ ፕሮዳክሽን ጋር በመሆኑ ድርጅቱ ለአርቲስቶቹ ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጥ አሳስቧል።

የሻኩራ ፕሮዳክሽን ኃላፊ ካሙዙ ካሳ በበኩላቸው የቀረበውን የውል ጥሰት ውንጀላ ያስተባበሉ ሲሆን “በስምምነቱ መሰረት ክፍያ እየፈጸምን ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

የተወሰነ ቀሪ ክፍያ መኖሩን ቢያምኑም ድርጅቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለአርቲስቶቹ ማከፋፈሉን ገልጸዋል።

ነገር ግን አርቲስቶቹ የተወሰኑ አባላት 50,000 ብር ያህል መጠነኛ ክፍያ ከመቀበላቸው ውጭ አብዛኛው ገንዘብ እንዳልተከፈላቸው ይከራከራሉ።

በ1978 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኪነት ቡድን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ ላደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ፤ ምስጋና ለማቅረብ “አደይ አበባ” (ህዝብ ለህዝብ) በሚል መሪ ሀሳብ ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት በመጓዝ የጥበብ ስራዎችን አቅርበው ነበር።

ከ39 ዓመታት በኃላ ደግሞ ኪን ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት በሚል መሪ ሀሳብ በዓይነቱና በይዘቱ ለየት ያለና የኢትዮጵያን ቱባ ባህልና ጥበብን ለዓለም ህዝብ ለማስተዋወቅ የባህልና የጥበብ ዲፕሎማሲ በመስራት የሀገራችንን መልካም ገፅታ የመገንባት ዓላማ ያነገበ ኩነት መጀመሩ ይታወሳል።

ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችን ያማከለ እና ትርዒቱ በሰርከስናና ባህላዊ ፍሽን ትርዒት ከዉብ የመድረክ ገፅታ ጋር የተላበሰ የተባለለት ኩነቱ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት በቀጣይነትም ኢትዮጵያን ጨምሮ ብራዚልን፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽና ኢንዶኔዥያን በአባልነት ባቀፈው የብሪክስ አባል አገራት እና በሌሎች የአለማችን ሐገራት በተከታታይነት እንደሚካሄድ በወቅቱ መገለጹ ይታወሳል።

A
ስለ ጸሐፊው

Administrator

12 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።