Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ኢትዮጲያ

በግል ትምህርት ቤቶች የክፍያ ጭማሪ እና ምዝገባ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

BS Bethelhem Solomon Jul 31, 2026 2 ደቂቃ ንባብ 22 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
በግል ትምህርት ቤቶች የክፍያ ጭማሪ እና ምዝገባ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

በ2019 የትምህርት ዘመን የክፍያ ጭማሪ ማድረግ የሚችሉት 166 የግል ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው


በአዲስ
አበባ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች 2019 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ሂደት፣ የክፍያ ጭማሪ እና የተለያዩ የግብዓት ጥያቄዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ።

ባለፉት ዓመታት የግል ትምህርት ቤቶች በሚጥሏቸው የወርሃዊ ክፍያ ዋጋዎች፣ የምዝገባ ዋጋዎች፣ የዩኒፎርም ሽያጮች እንዲሁም እንደ ሳሙና እና ሶፍት ባሉ በዓይነት በሚጠየቁ የትምህርት ቤት ግብዓቶች ምክንያት በወላጆች ዘንድ ሰፊ እና ተደጋጋሚ ቅሬታዎች ሲነሱ መቆየታቸው ይታወሳል።

የከተማ
አስተዳደሩ የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ የትምህርት ቤቶችን ወርሃዊ ክፍያ ጣሪያ በመወሰን ተቋማት በዘፈቀደ እና ያለ ገደብ ክፍያ እንዳይሰበስቡ የሚያስችል ጠንካራ አሰራር መዘርጋቱ የሚታወስ ነው።

በዚህም መሰረት አዲሱን የትምህርት ዘመን አስመልክቶ በተደረገው ማጣሪያ መሰረት 2019 የትምህርት ዘመን የክፍያ ጭማሪ ማድረግ የሚፈቀድላቸው በደንቡ መመሪያ መሰረት ከዚህ ቀደም ምንም አይነት ጭማሪ ያላደረጉ 166 የግል ትምህርት ቤቶች ብቻ መሆናቸውን የባለስልጣኑ ምክትል ስራ አስኪያጅ ታጋይቱ አባቡ  ገልጸዋል።

ምክትል ስራ አስኪያጇ አያይዘውም ከእነዚህ የተፈቀዱ ተቋማት ውጪ ያሉ ቀሪ ሁሉም የግል ትምህርት ቤቶች ምንም አይነት የክፍያ ጭማሪ ማድረግ በፍጹም እንደማይችሉ አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል።

Advertisement
Your ad could be here — contact us

ባለፈው ዓመትም በተደረጉ ተመሳሳይ ክትትሎች መመሪያውን በመጣስ በቅድመ አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ወላጆች ላይ የጽዳት መጠበቂያ እቃዎችን እና ወረቀት በዓይነት የጠየቁ 149 ተቋማት በክትትልና በወላጆች ጥቆማ በህግ ተለይተው እርምጃ እንደተወሰደባቸው ገልጸዋል።


ከዚህ
ቀደም በልዩ ልዩ ስም በዓይነት ይጠየቁ የነበሩ ግብዓቶች ሙሉ በሙሉ መመሪያውን የሚጥሱ እና ህገወጥ በመሆናቸው አሰራሩ እንዲቆም መደረጉንም አክለው ገልጸዋል።

ወላጆች እና አሳዳጊዎች ለአዲስ ተማሪዎች ምዝገባ የፈተና ክፍያን ጨምሮ ሌሎች ፈጽሞ ያልተፈቀዱ የክፍያ አይነቶች ሲጠየቁ እንዲሁም የተለያዩ ግብአቶችን በዓይነትና በገንዘብ እንዲያቀርቡ ሲገደዱ ነፃ የስልክ መስመር 9023 በመደወል ወይም በአካል ባለስልጣኑ መገኛ ድረስ በመቅረብ ፈጣን ጥቆማ ማቅረብ እንደሚችሉ ተገልጿል

በየዓመቱ የትምህርት ዘመን መጀመሪያ ወላጆችን እንቅልፍ የሚነሳው የትምህርት ቁሳቁስ መወደድ ብቻ ሳይሆን የግል ትምህርት ቤቶች 50 እስከ 100 በመቶ እና ከዚያ በላይ የሚያደርጉት ያልተገደበ የክፍያ ጭማሪ እንደሆነ ይታወቃል።ይህ ጫና በመጀመሪያዎቹ ቀናት ብቻ ሳያበቃ በዓላት እና የተለያዩ ተጨማሪ ቁሳቁሶችን በመጠየቅ ዓመቱን ሙሉ የሚቀጥል ነው።

ወላጆች የቤት ኪራይና ምግብን ለመሸፈን በሚታገሉበት ወቅት የትምህርት ቤት ክፍያ ከአቅም በላይ መሆኑን ሲያነሱ የግል ትምህርት ቤቶች በበኩላቸው የቤት ኪራይ ውድነትን፣ የኤሌክትሪክ እና የውሃ ታሪፍ መናርን፣ እንዲሁም ብቁ መምህራንን ለማቆየት ከፍተኛ ደመወዝ መክፈል ግድ መሆኑን እንደ ምክንያት ያነሳሉ።

ይሁን እንጂ ባለስልጣኑ ህጉን እና መመሪያውን በሚጥሱ ማንኛውም ተቋማት ላይ የሚደረገውን ጥብቅ የቁጥጥር ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል።

BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

56 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።