የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የዜጎችን የኑሮ ጫና ለመቀነስ እና በኪራይ ገበያው ላይ የሚስተዋሉ መደበኛ ያልሆኑ አሰራሮችን ለመግታት በማሰብ፤ ለ2019 በጀት ዓመት የሚተገበረው የቤት ኪራይ ዓመታዊ ጭማሪ ጣሪያ 11.5% ሆኖ እንዲጸድቅ መወሰኑን አስታውቋል።
ይህ ውሳኔ ቀደም ሲል በወጣው የቤት ኪራይ ቁጥጥር አዋጅ መሠረት የተወሰነ ሲሆን በከተማዋ የተካሄደ ሳይንሳዊ ጥናትንና የነዋሪውን የመክፈል አቅም ያገናዘበ መሆኑ ተገልጿል።
ይህንን ተከትሎ በመላው ከተማዋ የሚገኙ የግል መኖሪያ ቤቶች የአከራይ-ተከራይ አዲስ የውል እድሳት ምዝገባ ከዛሬ ሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ የቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች በይፋ መተግበር መጀመሩን ቢሮው አስታውቋል።
ይሁን እንጂ የዋጋ ጭማሪውና የውል እደሳቱ መነሻ የሚሆነው ከዚህ ቀደም በነበረው ውል ላይ የተቀመጠው የኪራይ ዋጋ ብቻ መሆኑን ቢሮው አፅንኦት ሰጥቶ ገልጿል።
ቢሮው አዲሱን የውል እድሳት ምዝገባ እና የተቀመጠውን የዋጋ ጣሪያ ወደ ጎን በመተው የሚፈጸሙ ማናቸውም ሕገ-ወጥ ድርጊቶች ላይ ጥብቅ ክልከላ ጥሏል።
በዚህም መሠረት በቢሮው ከተመዘገበው ውል እንዲሁም ከሚሰጠው አቅጣጫ ውጭ “ልዩ ውል” በሚል የሚፈጸሙ የመንደር ውሎች፣ ከሕጋዊ አሰራር ውጭ የሚደረጉ የአካባቢ ውሎች፣ እንዲሁም በጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) አካባቢ የሚደረጉ ማናቸውም ዓይነት ሕገ-ወጥ ውሎች ሙሉ በሙሉ የተከለከሉ ናቸው።
ማንኛውም አከራይ እና ተከራይ እነዚህን የተከለከሉ ሕገ-ወጥ ውሎች ይዘው ሲገኙ ወይም ከተቀመጠው የ11.5% የዋጋ ጭማሪ ጣሪያ በላይ ፈጽመው ከተገኙ ቢሮው ሕጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን አስጠንቅቋል።
የዋጋ ጭማሪውን እና አተገባበሩን በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ የሚገኙ ሲሆን የሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር አሻግሬ ዘውዱ ባለፉት ሁለት አመታት አከራይና ተከራይ በመነጋገር ግብር የሚታሰብበትን የኪራይ ገንዘብ በባንክ፣ የተቀረውን በግልጽ እየተቀበሉ እንደነበር በመጥቀስ፣ መንግስት ይህንን በአግባቡ መቆጣጠር እንዳልቻለ መግለጻቸው ይገኝበታል።
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው ጥናቱ የኑሮ ሁኔታን ያገናዘበና ሁለቱም ወገኖች የማይጎዱበት መሆኑን ይገልጻሉ።
ለዚህ ስራ የተመደቡ ኮሚቴዎች ያሉ በመሆኑ፤ በሚመጡ ጥቆማዎች መሰረት ችግሮችን እንደሚፈቱና አሰራሩን ለማዘመን እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።
አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ቤትን መከራየት እንዲችሉ መንግስት በራሱ ገንብቶ ቢያቀርብ፣ እንዲሁም የግል የቤት አልሚ ድርጅቶች ከሚሸጧቸው ቤቶች የተወሰኑትን እንዲያከራዩ የሚያስገድድ የህግ ማዕቀፍ ቢኖር እና የቤት አቅርቦቱ እንደልብ ካለ የተረጋጋ የኪራይ ዋጋ ሊኖር እንደሚችል ይታመናል።