የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ጂቡቲን የ"ታላቋ ሶማሊያ” አካል የሆኑ ክፍሎች በማለት መግለጫ መስጠታቸው ተሰምቷል።
ይህ ከፍተኛ የዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ያስነሳው ንግግር የተሰነዘረው ፕሬዝዳንቱ ሀገሪቱ ነጻነቷን ያገኘችበትን በዓል በማክበር ላይ በነበሩበት ወቅት ሲሆን ንግግሩ የሶማሊያን የድሮ የፓን-ሶማሊ ኢረደንቲዝም አስተሳሰብ እንደገና በማንቃት፤ በታሪክ ለከፍተኛ ግጭቶች ምክንያት የነበረውን ሃሳብ ያደሰ መሆኑ ተገልጿል።
ይህ አነጋጋሪ ንግግር የተሰነዘረበት ጊዜ አጠያያቂ መሆኑን ያነሱት ተንታኞች ሶማሊያ በአሁኑ ወቅት ከጎረቤት ሀገራት በተለይም ኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት እንደገና በመገምገም ላይ ትገኛለች ብለዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የገባችው ስምምነት በሞቃዲሾ ከፍተኛ ተቃውሞ እና ስጋት መፍጠሩ ይታወቃል።
በዚህ አውድ ውስጥ የፕሬዝዳንቱ "የጎደሉ ክፍሎች" ንግግር እንደ ተራ የንግግር ስልት ሳይሆን ያልተፈቱ ቅሬታዎችን የሚያንጸባርቅ ጠንካራ መልዕክት ሆኖ መታየቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በጉዳዩ ላይ ተንታኞች ሶስት ዋና ዋና ትንታኔዎችን የሰጡ ሲሆን ሶማሊያ ለረጅም ጊዜ በእርስ በእርስ ጦርነት የቆየችና የተከፋፈለች አገር በመሆኗ፤ ፕሬዝዳንቱ ይህንን አባባል የተጠቀሙት የሶማሊያ ህዝቦች ብሄራዊ ማንነታቸውን እንዲያስታውሱና በአንድነት እንዲሰባሰቡ ለማድረግ ነው ብለዋል።
ለሌሎች ታዛቢዎች ደግሞ የነጻነት በዓል ንግግሮች እንደ የፖሊሲ ሰነድ የሚታዩ አይደሉም፤ ይልቁንም በሶማሊያ የፖለቲካ ባህል ውስጥ ተደጋጋሚ እና የተለመደ የሀገራዊ ማንነት ማሳያ እንደሆኑ ገልጸዋል።
ሶስተኛው እና ይበልጥ አሳሳቢው ትንታኔ ደግሞ ይህ ንግግር ከሶማሊያ የውጭ ግንኙነት እና ከጎረቤት ሀገራት ጋር ካላት ስትራቴጂያዊ ግንኙነት አንጻር ከፍተኛ ስጋት የፈጠረ መሆኑን ያመላክታል።
የሶማሊያ አቋም እና ተጨባጭ ሁኔታ ትልቅ ክፍተት እንዳለበት መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን ፕሬዝዳንቱ እንደ "ጎደሉ ክፍሎች" የለዩዋቸው የኢትዮጵያ እና የኬንያ ድንበሮች በአሁኑ ወቅት ካሉ ዋና ዋና የውጭ ወታደራዊ ኃይሎች መካከል ናቸው።
ኢትዮጵያ በሶማሊያ ውስጥ ለአመታት በአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ በመሳተፍ፤ በአል-ሸባብ ላይ ጥቃት በመሰንዘር እና የሶማሊያ መንግስት ሊያቀርበው ያልቻለውን የጸጥታ መዋቅር በማጠናከር ቁልፍ ሚና ተጫውታለች።
ልክ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ፣ኬንያም በአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ስር በመሆን በሶማሊያ ሰላም እና ጸጥታ ለማስጠበቅ የተሳተፈች ሲሆን ሁለቱም ሀገራት በሶማሊያ ውስጥ ወሳኝ ሚና አላቸው።
ጂቡቲን በተመለከተ ሀገሪቱ ከፓን-ሶማሊያ አውድ ውጭ የራሷን ብሔራዊ ማንነት እና ከፍተኛ የጂኦፖለቲካዊ ጠቀሜታ የገነባች በመሆኗ የሶማሊያን የይገባኛል ጥያቄ እንደማትቀበል ተነግሯል።
በተጨማሪም ሶማሊያ በ1991 የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት የነበራትን ወታደራዊ ኃይል ሙሉ በሙሉ ያጣች ሲሆን ያንን ኃይልም ዳግም መገንባት አልቻለችም።
ፕሬዝዳንቱ የጠቀሷቸው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል፣ የኬንያ ሰሜን ምስራቅ ግዛት እና ጂቡቲ በየራሳቸው መንገድ የተረጋጉ እና በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ህጋዊ እውቅና ያላቸው በመሆናቸው ለማንኛውም አይነት የይገባኛል ጥያቄ ጠንካራ የሆነ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ምላሽ እንደሚሰጡ ተዘግቧል።
በመጨረሻም ይህ የሶማሊያ የይገባኛል ጥያቄ በታሪክ ውስጥ የሀገሪቱን ውድቀት ካመጡት አሳዛኝ የፖለቲካ አስተሳሰቦች ጋር የሚመሳሰል መሆኑ ተጠቅሶ ጉዳዩ ለሶማሊያ ህልውናም ሆነ ለቀጣናዊ ሰላም የራሱ የሆነ ስጋት እንዳለው ተንታኞች ገልጸዋል።