Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ኢትዮጲያ

የኤሌክትሪክ እና የውኃ ታሪፎች በገለልተኛ ባለሙያዎችና በህዝብ ተሳትፎ እንደገና እንዲሰሉ ተጠየቀ

BS Bethelhem Solomon Jun 19, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 244 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
የኤሌክትሪክ እና የውኃ ታሪፎች በገለልተኛ ባለሙያዎችና በህዝብ ተሳትፎ እንደገና እንዲሰሉ ተጠየቀ

በዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ላይ ተመስርተው በኢትዮጵያ ሊተገበሩ የሚችሉ ሶስት ቁልፍ ሞዴሎች ተጠቁመዋል።

በቅርቡ በመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ የተተገበሩት የታሪፍ ማሻሻያዎች የዜጎችን የመግዛት አቅም ያላገናዘቡና ለድህነት የሚዳርጉ በመሆናቸው በአስቸኳይ ታግደው እንደገና እንዲሰሉ ተጠይቋል።


ይህንን የጠየቀው የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ሲሆን መንግሥት የገጠመውን የሀብት እጥረትና የውጭ ምንዛሪ ጫና ቢረዳም መፍትሔው መላውን ሸማች ወደ ድህነት በሚገፋ የታሪፍ ጭማሪ ላይ ብቻ መመሥረት እንደሌለበት አሳስቧል።

ድርጅቱ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ባቀረበበት መግለጫው በመጀመሪያ ደረጃ በቅርቡ የተተገበሩት የኤሌክትሪክ፣ የውኃ፣ የፓስፖርት፣ የመንጃ ፈቃድ እና የተሽከርካሪ ሰሌዳ ታሪፎች በአስቸኳይ ታግደው፤ ከዜጎች የወቅቱ አማካይ ገቢና ከዝቅተኛው የደመወዝ ወለል አንፃር በገለልተኛ ባለሙያዎችና በሸማቾች ማኅበራት ተሳትፎ እንደገና የጋራ ሥሌት እንዲደረግባቸው ጠይቋል።


በየትኛውም የታሪፍ ማሻሻያ ሂደት ውስጥ በአዋጅ ቁጥር 813/2006 መሠረት ማሻሻያዎቹ ከመፅደቃቸው በፊት ከሸማቾች ማኅበራት፣ ከሲቪል ማኅበረሰብና ከባለሙያዎች ጋር ይፋዊና ግልጽ የሕዝብ ምክክር መካሄዱ የግዴታ መሆን እንዳለበት ድርጅቱ አፅንኦት ሰጥቷል።

የአገልግሎት ማምረቻ ወጪን ለመቀነስ በዘላቂነት ሊወሰዱ ይገባል ያላቸውን እርምጃዎች ሲዘረዝር  መንግሥት ለፓስፖርት ወረቀት፣ ለኤሌክትሪክና ለውኃ ቆጣሪዎች፣ እንዲሁም ለሰሌዳ ብረት ማምረቻ የሚሆኑ ጥሬ ዕቃዎችን ከማንኛውም የጉምሩክ ቀረጥና ቫት ነፃ በማድረግ ምርታቸውን በአገር ውስጥ እንዲያከናወኑ በማበረታታት የአቅርቦት ዋጋን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ እንደሚገባው ጠቁሟል።ይህ አሠራር የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትን ከመቀነሱም በላይ የአገር ውስጥ የሥራ ዕድልን እንደሚያሰፋም ተገልጿል።

Advertisement
Your ad could be here — contact us

ከዚህ ባሻገር የመንግሥት ተቋማት የራሳቸውን ዕዳና የኪሳራ ሸክም በደሃው ሕዝብ ኪስ ከመሸፈን ይልቅ በውስጣቸው ያሉትን ብልሹ አሠራሮች፣ ሙስናንና የአሠራር ብክነትን በማስወገድ የውስጥ ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ ጥሪ አቅርቧል።


በተጨማሪም በኤሌክትሪክ አገልግሎት ላይ እንደ መጀመሪያ ሙከራ የተጀመረው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች የመደገፍ አሠራር ተጠናክሮ በሌሎችም መሠረታዊ የአገልግሎት ዘርፎች ላይ እንደ መርህ ተግባራዊ ሊሆን ይገባል ተብሏል።

በመጨረሻም በዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ላይ ተመስርተው በኢትዮጵያ ሊተገበሩ የሚችሉ ሶስት ቁልፍ ሞዴሎችን የጠቆመው ድርጅቱ በአንደኝንነት የኬንያን ተሞክሮ ያቀረበ ሲሆን ይህም ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ያላቸውን ዜጎች ከማንኛውም የዋጋ ጭማሪ ነፃ የሚሆኑበትን የደኅንነት መረብ ታሪፍ ሥርዓትን መዘርጋት ነው።


ሁለተኛው የሩዋንዳ Irembo ዲጂታል መድረክ አሠራር ሲሆን የመንግሥትን ቢሮክራሲና የሰው ኃይል ወጪ በመቀነስ የአገልግሎት ዋጋን ማቃለል የሚል ነው።


በሶስተኛነት የተቀመጠው የቬትናም ተሞክሮ ሲሆን ከፍተኛ ፍጆታ ካላቸው ሃብታም ሸማቾችና ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ ታሪፍ በመሰብሰብ ዝቅተኛ ገቢ ላለው ዜጋ ድጎማ የሚያደርግ የአቋራጭ ድጎማ መርህን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል ተጠቁሟል።

BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

12 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።