Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

በኦሮሚያ ክልል የግል ሆስፒታሎች ላይ የደመወዝ ጣራ ተጣለ!

SM Samuel Mulgeta May 28, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 250 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
በኦሮሚያ ክልል የግል ሆስፒታሎች ላይ የደመወዝ ጣራ ተጣለ!

የደመወዝ ወለል ስታንዳርድ መፈጠሩ በግል ዘርፍ የሚሠሩ ዶክተሮች፣ ነርሶች፣ ፋርማሲስቶችና ላቦራቶሪ ባለሙያዎችን ከሕገ-ወጥ የጉልበት ብዝበዛ ለመከላከል እና የተሻለ የኑሮ ዋስትና ለመስጠት የታለመ

የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ በክልሉ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ የግል የጤና ተቋማት እና መድኃኒት መደብሮች ውስጥ የሚከናወኑ አዳዲስ የባለሙያዎችን ቅጥር እንዲሁም የደመወዝ ክፍያን በተመለከተ የመንግሥትን ቀጥተኛ ቁጥጥር የሚያጠናክር አዲስ እና ጥብቅ መመሪያ አስተላልፏል። 


ቢሮው በክልሉ ስር ለሚገኙ 21 የዞን የጤና መምሪያዎች በጻፈው ደብዳቤ መሠረት ከዚህ በኋላ በግል የጤና ዘርፍ ውስጥ የሚቀጠሩ አዲስ ባለሙያዎች የሚፈጽሙት የቅጥር ውል በየደረጃው በሚገኙ የመንግሥት የጤና መዋቅሮች ዕውቅና ሊሰጠው እንደሚገባ አዟል። 


በመመሪያው ላይ በሰፈረው ድንጋጌ መሠረት ማንኛውም የግል ሆስፒታል፣ ከፍተኛ እና መካከለኛ ክሊኒክ እንዲሁም የመድኃኒት መደብሮች አዲስ የሚቀጥሯቸው ባለሙያዎችን ሥራ ከጀመሩበት ቀን አንስቶ ሙሉ መረጃቸውን ለክልሉ ጤና ቢሮ በአስቸኳይ መላክ ይጠበቅባቸዋል። 

Advertisement
Your ad could be here — contact us


ይህ አሠራር በመንግሥት በኩል የባለሙያዎችን ዝውውር፣ የዕውቅና ማረጋገጫ ፈቃድ ትክክለኛነት እና የቅጥር ሁኔታን በቅርብ ለመከታተል ታስቦ የተዘጋጀ አዲስ የቁጥጥር ሥርዓት መሆኑ ተመላክቷል።


በሕክምናው ማኅበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት የሳበው የደብዳቤው ዋነኛ ድንጋጌ "በግል የጤና ተቋማትና መድኃኒት መደብሮች ውስጥ ለሚቀጠሩ አዲስ ባለሙያዎች የሚከፈላቸው ደመወዝ በመንግሥት የጤና ተቋማት ውስጥ ለሚሠሩ ባለሙያዎች ከሚከፈላቸው ደመወዝ ማነስ የለበትም" የሚለው ትዕዛዝ ነው። 


ይህ ማለት ደግሞ ማንኛውም የግል የጤና ተቋም የራሱን የገቢ አቅም ብቻ መነሻ በማድረግ ዝቅተኛ ደመወዝ የመወሰን መብቱ የተገደበ ሲሆን ቢያንስ ከመንግሥት ተቀጣሪዎች እኩል የመክፈል ግዴታ ተጥሎበታል ማለት ነው።


ይህ የደመወዝ ወለል ስታንዳርድ መፈጠሩ በግል ዘርፍ የሚሠሩ ዶክተሮች፣ ነርሶች፣ ፋርማሲስቶችና ላቦራቶሪ ባለሙያዎችን ከሕገ-ወጥ የጉልበት ብዝበዛ ለመከላከል እና የተሻለ የኑሮ ዋስትና ለመስጠት የታለመ መሆኑ ይገለጻል። 

 

ይህ የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ መመሪያ በድንገት የመጣ ሳይሆን ላለፉት ዓመታት በጤናው ዘርፍ ሲንከባለሉ የቆዩ ችግሮች የወለዱት ውሳኔን መነሻ በማድረግ ነው፡፡ 


ከእነዚህም መካከል በየዓመቱ የሚመረቁ ባለሙያዎች ቁጥር መጨመሩ እና የመንግሥት የቅጥር አቅም መገደቡ በርካታ ዶክተሮች እና ነርሶች በግል ተቋማት ውስጥ እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ክፍያ ለመሥራት እንዲገደዱ ማድረጉ ነው። 


በተጨማሪም መንግሥት በቅርቡ ያደረገውን የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ ለሠራተኞቹ የደመወዝ ጭማሪ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን የግል ዘርፉም ይሄንን ተከትሎ የባለሙያዎችን የደመወዝ ስኬል ካላስተካከለ በጤናው የሰው ኃይል ገበያ ላይ ከፍተኛ መዛባት ይፈጠራል የሚለው ይገኝበታል።


የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ለ21ዱም የዞን የጤና መምሪያዎች በላከው ደብዳቤ ማጠቃለያ ላይ እጅግ ጥብቅ የሆነ ማስጠንቀቂያ ያስቀመጠ ሲሆን በደብዳቤው ላይ የተጠቀሱትን አዳዲስ ትዕዛዞች፣ የቅጥር መመዘኛዎች እና የደመወዝ ስኬል ተፈጻሚ በማያደርጉ እና ሕጉን በሚጥሱ ማናቸውም የግል የጤና ተቋማት እና መድኃኒት መደብሮች ላይ አስፈላጊው ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ በግልጽ አስታውቋል።

SM
ስለ ጸሐፊው

Samuel Mulgeta

27 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።