Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ኢትዮጲያ

ለሴት አስተናጋጆች የወጣው ህግ!

SM Samuel Mulgeta May 23, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 353 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
ለሴት አስተናጋጆች የወጣው ህግ!

ይህ ደንብ አስተናጋጆች ከባህልና ከጨዋነት ያፈነገጠ አለባበስ እንዳይኖራቸው የሚከለክል ሲሆን በተጨማሪም በሚታዩ የሰውነት አካላት ላይ ንቅሳትን የሚከለክል፣ የወንዶች ጆሮ ጌጥን እና ከመጠን በላይ ሽቶ መጠቀምን የሚገድብ ነው፡፡

አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ ሆቴሎች፣ ምሽት ቤቶች እና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ በርካታ ሴት አስተናጋጆች በስራ ቦታቸው ላይ ከባድ የስነ-ልቦና እና የሰብአዊ መብት ጥሰት እየገጠማቸው መሆኑን በምሬት ይናገራሉ።



እነዚህ ሰራተኞች እንደሚገልጹት በተለይ ምሽት 12 ሰዓት ከሆነ በኋላ የየተቋማቱ ማናጀሮችና ባለቤቶች ደንበኞችን ለመሳብ እና ገበያ እንዲደራ በሚል ሴት አስተናጋጆቹ ሰውነታቸውን የሚያሳይ ወይም እጅግ አጫጭር ልብሶችን እንዲለብሱ ያስገድዷቸዋል።



ይህንን ትዕዛዝ የማይቀበሉ ሰራተኞች ደግሞ ከስራ እስከ መባረር የሚደርስ ጫና እና ማስፈራሪያ እንደሚደርስባቸው በመግለጽ በየቀኑ የስራ ቦታ ነጻነታቸውንና መብታቸውን ለማስከበር ከፍተኛ መከራ እየገጠማቸው መሆኑን በቅሬታ ሲያነሱ መስማት የተለመደ ነው።

Advertisement
Your ad could be here — contact us



ይህን በመስተንግዶ ዘርፉ ላይ የሚታየውን እና ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ጭምር ሰፊ መነጋገሪያ ሁኖ የቆየውን የተራቆተ አለባበስ ችግር ለመቅረፍ የአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነ-ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ የደንብ ልብስ አለባበስና አፈጻጸም ደንብ ቁጥር 178/2016ትን አውጥቶ ነበር።



ይህ ደንብ አስተናጋጆች ከባህልና ከጨዋነት ያፈነገጠ አለባበስ እንዳይኖራቸው የሚከለክል ሲሆን በተጨማሪም በሚታዩ የሰውነት አካላት ላይ መነቀስን የወንዶች ጆሮ ጌጥን እና ከመጠን በላይ ሽቶ መጠቀምን ይገድባል።



ደንቡን ተላልፈው የሚገኙና የሰራተኞቻቸውን አለባበስ የማያስተካክሉ ተቋማት ላይ መጀመሪያ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ በመቀጠል እስከ 50 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እንዲሁም ማስተካከያ ካላደረጉ ተቋማቱን እስከ ማሸግና የስራ ፍቃድን እስከ መሰረዝ የሚደርስ ጥብቅ ቅጣት ጥሏል።



ነገር ግን ይህ ጠንካራ ደንብ በይፋ ወጥቶ መተግበር ቢጀምርም አሁንም ድረስ በሴት አስተናጋጆች ላይ የሚደርሰው መገደድ ሙሉ ለሙሉ ሊቆም አልቻለም።



ደንቡ ከወጣ በኋላ የተወሰኑ መሻሻሎች ቢታዩም አሁንም በአንዳንድ ሆቴሎች ማናጀሮች እየመሸ ስለሆነ ምን ችግር አለው በማለት ሴት ሰራተኞችን አጫጭር ልብስ እንዲለብሱ የማስገደድ ድርጊቶች መቀጠላቸውን የኢትዮጵያ መስተንግዶ ባለሙያዎች ማኅበር አስታውቋል።



ለዚህ ደግሞ በምክንያትነት የተጠቀሰው ቀደም ሲል በየወረዳውና በክፍለ ከተማው የነበሩት የቁጥጥር መዋቅሮች በመታጠፋቸው በአሁኑ ሰዓት ደንቡን መሬት ላይ ወርዶ የሚከታተልና የሚቆጣጠር አካል መጥፋቱ ሲሆን ይህም ተቋማት ያለምንም ፍርሃት ህጉን እንዲጥሱና ሰራተኞችን እንዲበድሉ በር ከፍቷል።



በዚህም የአዲስ አበባ ከተማ ቱሪዝም ኮሚሽን የቁጥጥር መዋቅር ከከተማዋ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ጋር የተቀናጀ ግብረ-ኃይል በማቋቋም በተለይ በምሽት ሰዓት ድንገተኛ ፍተሻዎችን በማድረግ ህግ በሚጥሱ ማናጀሮችና ሆቴሎች ላይ በደንቡ የሰፈረውን 50 ሺህ ብሩን ቅጣትና የማሸግ እርምጃ እንዲወስዱ ተጠይቋል።



በተጨማሪም ሴት አስተናጋጆች የሚደርስባቸውን ጥቃት ያለምንም ፍርሃት የሚጠቁሙበት ነጻ የስልክ መስመር ተዘጋጅቶላቸው በቀጥታ ለመንግስት ድምፃቸውን የሚያሰሙበት ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባም ተጠቁሟል።



በመጨረሻም በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች መብታቸውን በጋራ ለመከላከል በማኅበራቸው ስር ይበልጥ መጠናከር ያለባቸው ሲሆን ህብረተሰቡም ሆነ ደንበኞች የአገልግሎት ቦታዎችን በሚመርጥበት ወቅት ሴቶችን እንደ ደንበኛ መሳቢያ ለሚጠቀሙ ሆቴሎች እውቅና ባለመስጠትና የአገልግሎት ጥራትን ብቻ መስፈርት በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነት መወጣት እንደሚገባ ተጠቁሟል።

 

 

SM
ስለ ጸሐፊው

Samuel Mulgeta

27 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።