በኬኒያ የነዳጅ ዋጋ ታሪካዊ የተባለለትን ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ተከትሎ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ እና በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች መጠነ-ሰፊ ሕዝባዊ ተቃውሞ እና ሀገር አቀፍ አድማ ተቀስቅሷል።
በዚህ አድማ ሳቢያም በርካታ ተጓዦች በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎችና መንገዶች ላይ የተስተጓጎሉ ሲሆን ሰልፈኞች በዋና ዋና አውራ ጎዳናዎች ላይ ጎማዎችን በማቃጠል መንገዶችን ዘግተዋል።
የሕዝብ ማጓጓዣ ሚኒባሶች ባለቤቶች ማኅበር፣ የሞተር ሳይክል ነጂዎች፣ የጭነት መኪና አሽከርካሪዎች እና የዲጂታል ታክሲ ማኅበራትን ጨምሮ በዘርፉ ያሉ መዋቅሮች በሙሉ በወሰኑት የጋራ አቋም መሠረት የትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ቆሟል።
ጥምረቱ ትናንት እሑድ ባወጣው የጋራ መግለጫ የአድማው ዓላማ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ለመቃወም መሆኑን ገልጾ በሀገሪቱ ታሪክ ትልቁ የተባለለትን የተቀናጀ እርምጃ መጀመሩን አረጋግጧል።
በተጨማሪም ይህ እርምጃ ለትራንስፖርት ኦፕሬተሮች ብቻ ሳይሆን ለእያንዳንዱ የኬኒያ ዜጋ የተደረገ ጥሪ መሆኑን አስታውቆ የነዳጅ ዋጋ መጨመር የመጨረሻው ሰለባ የሚያደርገው ነዋሪውን በመሆኑ የትራንስፖርት፣ የምግብ፣ የኤሌክትሪክ እና መሠረታዊ ቁሳቁሶች ዋጋ እንዲናር ያደርጋል ብሏል።
በአድማው ላይ የሕዝብ ትራንስፖርት ዘርፍ ፌዴሬሽን፣ የኬኒያ አሽከርካሪዎች ማኅበር፣ የጭነት መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበር እና የዲጂታል ታክሲዎች ማኅበርን ጨምሮ በርካታ ተጽዕኖ ፈጣሪ የዘርፉ ማኅበራት የተሳተፉ ሲሆን ይህም አድማው 99 በመቶ ስኬታማ እንዲሆን እንዳደረገው ጥምረቱ ገልጿል።
የግል ተሽከርካሪ አሽከርካሪዎች በበኩላቸው ከቤት አለመውጣትን የመረጡ ሲሆን የግል ትምህርት ቤቶች ማኅበርም ለአባላቱ ባስተላለፈው የደኅንነት ሥጋት ምክረ-ሀሳብ መሠረት አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ውሎአቸውን ወደ ኦንላይን ትምህርት ቀይረዋል ተብሏል።
ይህ ሕዝባዊ ቁጣ የተቀሰቀሰው ባለፈው ዓርብ በኬኒያ የነዳጅ ዋጋ ታሪካዊ የተባለለትን ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ተከትሎ ሲሆን በዚሁ የዋጋ ክለሳ መሠረት የናፍጣ ዋጋ በ23.5 በመቶ፣ የቤንዚን ዋጋ ደግሞ በ8 በመቶ አድጓል።
ይሁን እንጂ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በአሁኑ ወቅት ከኬንያ ውጭ የሚገኙት ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በጉዳዩ ላይ የሰጡት አስተያየት የለም። ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ወር የዋጋ ክለሳ ወቅት ጭማሪውን ከኢራን ጦርነት ጋር ቢያያይዙትም ያኔ ከፍተኛ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ታክስ መቀነሳቸው ይታወሳል።
የኬኒያ ብሔራዊ የንግድና ዘርፍ ምክር ቤት (KNCCI) በበኩሉ ይህ የነዳጅ ዋጋ መጨመር በሀገሪቱ ባሉ ሁሉም ዕቃዎችና አገልግሎቶች ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አስጠንቅቋል። ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ የኤፕሪል እና ሜይ ወራት ንጽጽር እንደሚያሳየው በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ድፍድፍ ዋጋ ያደገው በ10.7 በመቶ ብቻ ቢሆንም በኬኒያ የናፍጣ ዋጋ ግን በ23.5 በመቶ ጨምሯል።
ከሥልጣናቸው ከተነሱ በኋላ ተቃዋሚ ጎራውን የተቀላቀሉት የሀገሪቱ የቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪጋቲ ጋቻጓ በበኩላቸው ለዚህ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ተጠያቂዎቹ ከፍተኛ ትርፍ የሚፈልጉ ሙሰኛ ነጋዴዎች ናቸው ሲሉ ወቅሰዋል።
ጋቻጓ የኬኒያን የነዳጅ ዋጋ የወደብ አገልግሎት ለማግኘት በኬኒያ ላይ ከሚደገፉት እንደ ኡጋንዳ ካሉ የጎረቤት የየብስ ሀገራት ጋር በማነጻጸር በኡጋንዳ ያለው የነዳጅ ዋጋ ከኬኒያ ያነሰ መሆኑን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።
ኬኒያ በሞምባሳ ወደብ በኩል ወደ ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎችን በየብስ ትራንስፖርት ለሚያጓጉዙ የቀጣናው ነጋዴዎች ዋነኛ የትራንስፖርት ማዕከል በመሆን የምታገለግል ሀገር ናት።