Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ቢዝነስ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሁሉንም ቀጥተኛ ያልሆኑ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎች ሊጠቀም መሆኑን አስታወቀ

BS Bethelhem Solomon Nov 3, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 65 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሁሉንም ቀጥተኛ ያልሆኑ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎች  ሊጠቀም መሆኑን አስታወቀ

ምግብ ነክ ያልሆነ የዋጋ ንረት ከ12.2 በመቶ ወደ 15.1 በመቶ ከፍ ማለቱም ተገልጿል


የኢትዮጵያ
ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል እና የፖሊሲ ወለድ ምጣኔ ባለበት እንዲቆይ መወሰኑን አስታውቋል።


ብሔራዊ ባንኩ ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 24፤ 2019 ባካሄደው የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ስምንተኛ ስብሰባው ላይ ሶስት የፖሊሲ ምክረ ሃሳቦችን ያቀረበ ሲሆን፤ እየታየ ባለዉ መጠነኛ ልቅ የገንዘብና ፋይናንስ ሁኔታ የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ወለድ ምጣኔ ባለበት 16 በመቶ ሆኖ እንዲቀጥል እና የ±3 በመቶኛ ነጥብ ልዩነት ክልል ሳይለወጥ እንዲቆይ ወስኗል፡፡


ብሄራዊ ባንኩ የወደፊት የዋጋ ግሽበት አዝማሚያን በተመለከተ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የትንበያ ጊዜ እየቀነሰ የሚሄድ ቢሆንም በድርብ አሃዝ ዉስጥ እንደሚቆይ ገምቷል። ይህን ተከትሎም የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲን ማስቀጠል አስፈላጊ እንደሆነ ጠቅሷል።


የገንዘብ ፖሊሲውን ለማስጠበቅም ሁሉንም ቀጥተኛ ያልሆኑ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎችን ይጠቀማል ያለው ማዕከላዊ ባንኩ በተለይም በኢኮኖሚው ውስጥ ከሚጠቀበቀው በላይ ትርፍ ገንዘብ ሲኖር ባንኩ ከባንኮች ጋር የሚያደርገውን የጨረታ ሰነድ-ግብይት እንደሚጠቀም አክሏል።


የምግብ ዋጋ ግሽበት በሰኔ ወር 2018 ከተመዘገበው 15.1 በመቶ ወደ 14.8 በመቶ በመጠኑ የቀነሰ ሲሆን፣ ምግብ ነክ ያልሆነ የዋጋ ግሽበት ደግሞ ከ12.2 በመቶ ወደ 15.1 በመቶ ከፍ ማለቱን አስታውቋል። ለዚህም በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ሳቢያ ከአቅርቦት ጋር የተያያዘ እንደሆነ አመክቷል።


በምግብ ዋጋ ግሽበት ረገድ የዳቦና የእህል ምርቶች፣ የአትክልትና ጥራጥሬ ምርቶች፣ እንዲሁም የቡና ዋጋ መጨመር ለዋጋ ግሽበቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልጾ ለምግብ ነክ ያልሆኑ ዕቃዎች ጭማሪ ደግሞ በተለይም የኤሌክትሪክ ታሪፍ፣ የኬሮሲን እና የማገዶ እንጨት ዋጋ መጨመር ምክንያት እንደሆኑ አስቀምጧል።


የብድር ዕድገት ላይ ተጥሎ የነበረው ገደብ ቢነሳም እና ባንኮች ከፍተኛ ቁጠባ ቢሰበስቡም፤ የሰጡት አዲስ ብድር ከአጠቃላይ ተቀማጭ እና ተመላሽ ሲነጻጸር እድገት አለማሳየቱን እና ከባለፈው ሩብ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ተቀራራቢ መሆኑን ገልጿል።


የመንግስት ግምጃ ቤት ሰነዶች አማካይ የወለድ ምጣኔ እና ባንኮች እርስ በእርስ የሚበዳደሩበት የ7-ቀን የባንክ ለባንክ የገንዘብ ገበያ አማካይ የወለድ ተመኖች ከግንቦት ወር 2018 ጀምሮ ማሽቆልቆል ማሳየታቸውንም አክሏል። ለዚህም ሌሎች ምክንያቶች እንዳሉ ሆኖ ዋነኛው ባንኮች በብሔራዊ ባንክ ያላቸዉ ትርፍ ገንዘብ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ እንደሆነ ነው።



ብሔራዊ ባንኩ እየተገበረዉ የሚገኘው መደበኛ የባንኮች የመጠባበቂያ ተቀማጭ እንዳለ ሆኖ፤ የብድር ዕድገት መስፋፋት በዋጋ ግሽበት ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድር ሆኖ ሲገኝ፣ በሚያካሂደው መደበኛ ግምገማ መሠረት የእያንዳንዱን ባንክ የብድርና የተቀማጭ ሂሳብ ጥመርታ ላይ በመመርኮዝ የተለየ የመጠባበቂያ ተቀማጭ መተግበሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ምክረ ሃሳቡን አቅርቧል።

BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

92 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።