Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

ፌስቡክ እና ኢንስታግራም አሰራራቸውን ሊቀይሩ እንደሚችሉ ተጠቆመ

BS Bethelhem Solomon Aug 17, 2026 1 ደቂቃ ንባብ 65 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
ፌስቡክ እና ኢንስታግራም አሰራራቸውን ሊቀይሩ  እንደሚችሉ ተጠቆመ

ሜታ ታዳጊዎችን ለአደጋ እና ለማህበራዊ ሚዲያ ሱሰኝነት የሚያጋልጡ አሰራሮችን ተጠቅሟል በሚል ከ30 የአሜሪካ ግዛቶች ክስ ቀረቦበታል


ኢንስታግራም እና ፌስቡክን የሚያስተዳድረው ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሜታ ታዳጊዎችን ለአደጋ እና ለማኅበራዊ ሚዲያ ሱስ የሚያጋልጡ አሠራሮችን ተጠቅሟል በሚል ከአሜሪካ 30 ግዛቶች የቀረበበት ክስ በፍርድ ቤት ሊታይ መሆኑ ተገልጿል።

ክሱ ከተረጋገጠ በኢንስታግራም እና ፌስቡክ የሚገኙ እንደ 'ላይክ'፣ ኢንፋይናይት ስክሮል፣ አውቶፕሌይ እና ተደጋጋሚ ኖቲፊኬሽን ያሉ ባህሪያት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ሊደረግ ይችላል ተብሏል።

ካሊፎርኒያ እና ኒውዮርክን ጨምሮ 30ዎቹ የአሜሪካ ግዛቶች ሜታ ታዳጊዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎቹ ላይ ረዥም ሰዓት እንዲቆዩና ደጋግመው ወደ መተግበሪያዎቹ እንዲመለሱ የሚያደርጉ አሠራሮችን በመጠቀም የታዳጊዎችን ደኅንነት አልጠበቀም ሲሉ ከሰዋል። 

Advertisement
Your ad could be here — contact us

በተለይም የማኅበራዊ ሚዲያ አሠራሮች ተጠቃሚዎች አንድ ይዘት ካዩ በኋላ ተመሳሳይ ወይም ሌላ አሳታፊ ይዘት ወዲያውኑ እንዲያዩ በማድረግ ተጠቃሚውን በመተግበሪያው ላይ እንዲቆይ የሚያበረታቱ ናቸው የሚል ክርክር ቀርቦበታል።

ከክሱ ዋና ነጥቦች አንዱ 'ላይክ' ሲሆን በተለይ ታዳጊዎች የሚያገኙትን የ'ላይክ' ብዛት ከሌሎች ጋር በማወዳደር ለራሳቸው የሚሰጡት ዋጋ ከማኅበራዊ ሚዲያ ምላሽ ጋር እንዲቆራኝ ሊያደርግ ይችላል ተብሏል። ይህም የብቸኝነት፣ የመገለል ስሜት፣ የሰውነት ገጽታን በተመለከተ የተዛባ አመለካከት እና ሌሎች አሉታዊ ስሜቶችን ሊያባብስ እንደሚችል ተጠቁሟል። 


የአሜሪካ ግዛቶቹ ፍርድ ቤት ሜታ በታዳጊዎች አጠቃቀም ላይ ጥብቅ ለውጦችን እንዲያደርግ እንዲያዝ ሲጠይቁ ከእነዚህም ታዳጊዎች የሚጠቀሙበትን አካውንት ቤተሰቦች እንዲቆጣጠሩ የሚያስችል ሥርዓት ማጠናከር እና የማያቋርጥ ኢንፋይናይት ስክሮል አሠራርን መገደብ ተካቷል። 

በተጨማሪም አንድን መረጃ አስከትሎ ሌላ ዶፓሚን ሆርሞንን የሚያነቃቃ መረጃ አለመስጠት፣ የሰዎችን ገጽታ መለወጥ የሚችለውን ፊልተር ማቆም፣ የ‘ላይክ’ ቁጥርን እንዳይታይ ማድረግ ብሎም ቪድዮዎች በራሳቸው እንዲጫወቱ የሚያደርገውን አውቶፕሌይ ማቆም የሚለውም ይገኝበታል። 

እንዲሁም ተጠቃሚዎች ብዙ አካውንቶችን እንዳይከፍቱ መገደብ እና ታዳጊዎችን በተደጋጋሚ ኖቲፊኬሽን ወደ መተግበሪያዎቹ እንዲመለሱ የሚያደርጉ አሠራሮችን መቀነስ እንደሚኖርበትም ተጠይቋል። 

ሆኖም ሜታ ክሱን ያልተቀበለ ሲሆን ኩባንያው ታዳጊዎችን ለመደገፍ የረዥም ጊዜ ቁርጠኝነት እንዳለው ገልጾ፣ በፍርድ ቤት የቀረቡትን ክሶች በማስረጃ እንደሚቃወም አስታውቋል።

ሜታ በተጠየቀው መሠረት አሠራሩን እንዲቀይር ከተወሰነ ኢንስታግራምና ፌስቡክ ከሚታወቁበት በእጅጉ የተለዩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተገምቷል። ኩባንያው በቅርቡ ኒው ሜክሲኮ ውስጥ በተካሄደ ሌላ የፍርድ ሂደት 942 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍል ተወስኖበታል።

BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

67 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።