የትምህርት ሚኒስቴር የመንግስት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች እና ምክትል ፕሬዚዳንቶች ምልመላ ከዚህ ቀደም ከነበረው የአካዳሚክ ማህበረሰብ ብቻ የመመረጥ ልምድ ወጥቶ፤ በውድድር እና በብቃት ላይ በተመሰረተ አዲስ አሰራር እንዲከናወን የሚደነግግ መመሪያ ይፋ አድርጓል።
አዲሱ መመሪያ ቁጥር 1146/2018 ለመጀመሪያ ጊዜ ከዩኒቨርሲቲ ውጭ ባሉ የመንግስት እና የግል የኢንዱስትሪ ዘርፎች የሚሰሩ ልምድ ያላቸው ከፍተኛ አመራሮች ለዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትነት እንዲወዳደሩ ዕድል ከፍቷል።
ይህ አሰራር የዩኒቨርሲቲዎችን የአስተዳደር አቅም፣ የሥራ አመራር ብቃት እና ተጠያቂነትን ለማሻሻል ያለመ ሲሆን ውድድሩ ተወዳዳሪዎችን በሦስት ዋና ዋና መስፈርቶች ይገመግማል ተብሏል።
በዚህም የትምህርት ዝግጅት 30 በመቶ፣ የአመራር ልምድ 30 በመቶ እና ስትራቴጂክ ዕቅድ አቀራረብ 40 በመቶ ድርሻ እንዲኖራቸው ተደርጓል።
በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ቴክኖሎጂን፣ የፋይናንስ አስተዳደርን፣ የሀብት ማሰባሰብን እና ተቋማዊ ለውጥን ለማምጣት በማሰብ ከዩኒቨርሲቲ ውጭ ያሉ የኢንዱስትሪ አመራሮች ለቦታው እንዲወዳደሩ ፈቃድ መሰጠቱም ነው የተገለጸው።
የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪዎች በዩኒቨርሲቲው መጠን ልክ የሆነ በጀት እና የሰው ኃይል የማስተዳደር ልምድ ሊኖራቸው እንደሚገባ በመመሪያው ተገልጿል።
ምልመላውን በግልጽነት ለማካሄድ ሁለት ኮሚቴዎች የተቋቋሙ ሲሆን የመጀመሪያው አራት አባላት ያሉት ኮሚቴ ሲሆን ብቁ እጩዎችን የመለየትና የመጋበዝ ኃላፊነት አለበት ተብሏል።
ሁለተኛው ሰባት አባላት ያሉት የምልመላ እና ምርጫ ኮሚቴ ሲሆን የቦርድ፣ የሴኔት፣ የተማሪዎች ህብረት፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የውጭ ምርምር ተቋማት እና የሰው ኃይል አስተዳደር ተወካዮችን ያካተተ ነው።
የሥራ ቦታ ማስታወቂያዎች በየመገናኛ ብዙሃኑ ለ22 የሥራ ቀናት የሚቆዩ ሲሆን፤ አጠቃላይ ሂደቱ በ4 ወራት ውስጥ መጠናቀቅ እንዳለበት ያስታወቀው ሚንስትሩ ለፕሬዚዳንትነት የተመረጡት እጩዎች ለ6 ዓመታት እንደሚያገለግሉ እና በየስድስት ወሩ በአስተዳደር ቦርድ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እንደሚደረግባቸው ጠቅሷል።
በተከታታይ ሁለት ጊዜ ከ60 በመቶ በታች ያመጡ አመራሮች ከኃላፊነታቸው የሚነሱ ሲሆን "እጅግ ከፍተኛ" አፈጻጸም ያላቸው ብቻ በትምህርት ሚኒስቴር ፈቃድ ያለምንም ውድድር ለሁለተኛ ጊዜ የመመረጥ ዕድል እንደሚያገኙ ተገልጿል።የዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንቶችም ተመሳሳይ የሆነ የአፈጻጸም ግምገማ እና የሁለተኛ ጊዜ የመመረጥ እድል ይኖራቸዋል።
ይህ እርምጃ የተወሰደው የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ዘመናዊ የምርምር ውጤት ለማምጣት፣ የፋይናንስ ዘላቂነትን ለማረጋገጥ እና ከኢንዱስትሪው ጋር ያላቸውን ትስስር ለማጠናከር እየገጠሟቸው ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ነው።
መንግስት በዚህ አዲስ አሰራር የዩኒቨርሲቲዎችን የአመራር ብቃት ለማሳደግ ያለመ ሲሆን፣ በየትምህርት ተቋማቱ የሚመረጡት አመራሮች ተቋማዊ ተግዳሮቶችን የመፍታት አቅም ያላቸው ስትራቴጂክ ዕቅዶችን እንዲያቀርቡ ይጠበቃል።
ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩ ግለሰቦች ቢያንስ የመምህርነት (Assistant Professor) ማዕረግ ሊኖራቸው የሚገባ ሲሆን፣ ሴት ተወዳዳሪዎችን ለማበረታታት በማስተርስ ዲግሪ እንዲወዳደሩ የተለየ ሁኔታ ተመቻችቷል።
ለዚህ ቦታ የሚወዳደሩት ቢያንስ የሁለት ዓመት ፕሬዚዳንትነት፣ የሦስት ዓመት ምክትል ፕሬዚዳንትነት ወይም የሦስት ዓመት የኮሌጅ ዲንነት ልምድ ሊኖራቸው የሚገባ ሲሆን የምክትል ፕሬዚዳንቶች የአካዳሚክ እና የምርምር አመራሮች የዶክትሬት ዲግሪ፣ የአስተዳደር እና ቢዝነስ ልማት አመራሮች ደግሞ ቢያንስ የማስተርስ ዲግሪ ሊኖራቸው ይገባል።
ይህ መመሪያ በፍትህ ሚኒስቴር ተመዝግቦ በየትምህርት ሚኒስቴሩ ድረ-ገጽ እንደታተመ ወዲያውኑ ተግባራዊ ይሆናል።