በሀገር አቀፍ ደረጃ ለረዥም ጊዜ ሲያነሷቸው ከነበሩት 12 መሰረታዊ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የሆነው የትርፍ ሰዓት ክፍያ ምላሽ እንዳላገኘ የጤና ባለሙያዎች ተናግረዋል።
በዚህም የፌደራል መንግሥት ወጥነት ያለው የአከፋፈል መመሪያ ቢያወርድም በክልሎች ደረጃ በሚታይ የበጀት እጥረትና የአፈጻጸም መጓደል ሳቢያ ባለሙያዎች ለከፍተኛ እንግልት እየተዳረጉ መሆኑ ታውቋል።
በአማራ ክልል የጤና ተቋማት የሚገኙ ባለሙያዎች ለስድስት ወራት የቆየ የትርፍ ሰዓት ውዝፍ ክፍያ እንዳልተከፈላቸው የገለጹ ሲሆን የክልሉ መንግሥት በበኩሉ የበጀት እጥረት መኖሩን በመጥቀስ የጤና ተቋማት እንደ አቅማቸው እንዲከፍሉ መፍቀዱ ክፍያውን ወጥነት የለሽ እና አድሎአዊ እንዳደረገው ተሰምቷል።
በተለይም በምሥራቅ ጎጃም ዞን ለተቃውሞ ድምጻቸውን ያሰሙ አምስት ባለሙያዎች ለእስር መዳረጋቸውና በሌሎችም አካባቢዎች ተመሳሳይ ዛቻዎች መኖራቸው የአገልግሎት አሰጣጡን ለከፍተኛ ቀውስ ዳርጎታል ተብሏል።
በሌላ በኩል የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ክፍያ ያልተፈጸመላቸው ባለሙያዎች ክፍያ በአስቸኳይ እንዲፈጸም ጥብቅ መመሪያ አስተላልፏል።
ቢሮው የክፍያ አፈጻጸሙ ወጥ ባልሆነ መንገድ ሲፈጸም መቆየቱን በማመን ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ቢጠቁምም፤ በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ የቅሬታ ድምፆች እየተሰሙ ነው።
እንደ ደቡብ ኢትዮጵያ ባሉ አካባቢዎች የደመወዝ ክፍያ መስተጓጎል የጤና አገልግሎቱን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያሽቆለቁል አድርጎታል።
ይህንን የክፍያ መቆራረጥ እና የአፈጻጸም ክፍተት የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ አረጋግጠዋል።
ሚኒስትሯ ባለሙያዎች ትዕግስት እንዲያደርጉና አገልግሎቱን እንዳያቋርጡ አሳስበው፤ የጤና ተቋማት አመራሮች የራሳቸውን አማራጭ ሀብት አፈላልገው ክፍያውን እንዲፈጽሙ አቅጣጫ ሰጥተው ነበር።
በተመሳሳይ የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1353/2017 ሥልጣኑን በመጠቀም፤ “የመንግሥት ጤና ተቋማት ሠራተኞች የትርፍ ሰዓት የሚፈቀድበት ሁኔታ እና ክፍያ ለመወሰን የወጣ መመሪያ ቁጥር 1119/2018” ተግባራዊ እንዲሆን ማድረጉ ይታወሳል።
መመሪያው ለአገልግሎት ጥራት ሲባል በአንድ ወር ውስጥ ከ212 ሰዓት በላይ የትርፍ ሰዓት ሥራ እንዳይሠራ ገድቦ በምሽት፣ በሳምንቱ መጨረሻ እና በበዓላት ለሚሠሩ ባለሙያዎች ክፍያ በመደበኛ የደመወዝ ስሌት ተባዝቶ እንዲከፈል እንዲሁም የሕክምና ባለሙያዎችን ብቻ ሳይሆን የአስተዳደር ሠራተኞችንም ማካተትን እንደ ዋና ዓላማ ይዞ ነበር።
ይሁን እንጂ ይህ በፌደራል ደረጃ የወጣው ወጥ መመሪያ ክልሎች በሚያቀርቡት “የበጀት እጥረት” ሰበብ በተግባር ሊውል ባለመቻሉ የጤና ተቋማት በየፊናቸው በሚያደርጉት የተለያየ የአከፋፈል ሥርዓት ምክንያት ባለሙያዎች ለከፍተኛ ምሬት ተዳርገዋል።
በዚህም የጤና ባለሙያዎች የሥራ መልቀቅና የባለሙያዎች እጥረት በጤና ተቋማት ላይ እየተባባሰ መምጣቱ የአገልግሎት ጥራቱን በእጅጉ እየጎዳው መሆኑን የሕክምና ማኅበራትን ጨምሮ የተለያዩ የዘርፉ ባለሙያዎች እየተናገሩ ይገኛሉ።