Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ቢዝነስ

ቶታል ኢነርጂስ ከ76 ዓመት በኋላ ከኢትዮጵያ ገበያ ወጣ

BS Bethelhem Solomon Jul 2, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 929 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
ቶታል ኢነርጂስ ከ76 ዓመት በኋላ ከኢትዮጵያ ገበያ ወጣ

ኦላ ኢነርጂ ግሩፕ ንብረቶች ሙሉ በሙሉ በመግዛት በኢትዮጵያ የነዳጅ ማከፋፈያ ዘርፍ ውስጥ ትልቁ የውጭ ሀገር ኩባንያ ሆኗል

የሊቢያው ኦላ ኢነርጂ ግሩፕ ለሰባት አሥርተ ዓመታት በኢትዮጵያ የነዳጅ ዘርፍ ሲንቀሳቀስ የቆየውን የፈረንሳይ ግዙፍ ኩባንያ ቶታል ኢነርጂስ ንብረቶች በሙሉ መግዛቱን ይፋ ድርጓል


በፓሪስ በተፈረመው ስምምነት መሠረት ኦላ ኢነርጂ፤ ቶታል ኢነርጂስ በኢትዮጵያ የነበረውን የነዳጅ ማከፋፈያና ተያያዥ ንብረቶች በሙሉ በመረከብ በሀገሪቱ የነዳጅ ችርቻሮ ገበያ ውስጥ ትልቁ የውጭ ሀገር ኩባንያ ሆኗል።


ይህ ስምምነት ቶታል ኢነርጂስ 1950ዎቹ ጀምሮ በኢትዮጵያ የጀመረውን 76 ዓመታት የሥራ ጉዞ እንዲያጠናቅቅ አድርጓል።

ስምምነቱ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ወደ 120 የሚጠጉ የነዳጅ ማደያ ጣቢያዎችን እና በዱከም የሚገኘውን 13 ሺህ ሜትር ኩብ አቅም ያለው የነዳጅ እና የጋዝ ማከማቻ ተርሚናልን በባለቤትነት ያስተላልፋል።


በፓሪስ በተከናወነው የፊርማ ሥነ ሥርዓት ላይ የሊቢያው የነዳጅ እና ጋዝ ሚኒስትር ኻሊፋ አብዱልሳዲቅ የቶታል ኢነርጂስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፓትሪክ ፑያኔ እንዲሁም የኦላ ኢነርጂ ሊቀመንበር አቡዘድ ሱዋሌም ተገኝተዋል።


ምንም እንኳን ግብይቱ ለኢትዮጵያ የነዳጅ ዘርፍ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ነው ቢባልም ለግዢው የወጣው የገንዘብ መጠን በይፋ አልተገለጸም።

ኦላ ኢነርጂ ከሊቢያ ብሔራዊ ኢንቨስትመንት ፖርትፎሊዮ (LAIP) ስር የሚተዳደር ሲሆን በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ 17 ሀገራት ውስጥ 1,300 በላይ ማደያዎች ያሉት ግዙፍ የኢነርጂ ተቋም ነው።


ኩባንያው ከዚህ ቀደም በነበሩት ሁለት አሥርተ ዓመታት ውስጥ እንደ ሼል እና ኤክሶን ሞቢል ያሉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ይቆጣጠሯቸው የነበሩ የችርቻሮ መረቦችን በመግዛት በአህጉሪቱ መስፋፋቱን ቀጥሏል።


የሊቢያ መንግሥት ይህንን ግዢ በአህጉሪቱ ያለውን የኢኮኖሚ ተጽዕኖ ለማስፋት እና ብሔራዊ የኢንቨስትመንት አቅምን ለማጠናከር እንደ ትልቅ ስትራቴጂያዊ እርምጃ እንደሚወስደው የተገለጸ ሲሆን ባለፈው ዓመት ብቻ ኩባንያው 34.5 ሚሊዮን ዩሮ የተጣራ ትርፍ ማግኘቱ የሚታወስ ነው።

Advertisement
Your ad could be here — contact us

ቶታልኢነርጂስ በኢትዮጵያ በነበረው ቆይታው ከነዳጅ ማከፋፈያ ባለፈ በዱከም የሚገኘውን ትልቅ የነዳጅ እና የጋዝ ማከማቻ በመጠቀም ለአገሪቱ ኢንዱስትሪዎች ወሳኝ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።


በተጨማሪም እንደ ቶታል ስታርትአፐር ኦፍ ይር ያሉ ሥራ ፈጠራን የሚያበረታቱ ፕሮግራሞችን እና የትራፊክ ደህንነት ዘመቻዎችን በኢትዮጵያ በማከናወን ረጅም ጊዜ ያሳለፈ ሲሆን ከኢትዮጵያ ገበያ መውጣቱ የነበረውን የሰባት አሥርተ ዓመታት የንግድ ታሪክ ማጠቃለያ ተደርጎ ተወስዷል።

ይህ ስምምነት የተፈጸመው የኢትዮጵያ መንግሥት በነዳጅ ማከፋፈያ ዘርፍ አዳዲስ ማሻሻያዎችን እና የገበያ ድርሻ ቀመሮችን በመተግበር ላይ ባለበት ወሳኝ ወቅት ነው።


የኢትዮጵያ የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለሥልጣን የዘርፉን አቅርቦት ሰንሰለት ለማስተካከል በክልላዊ የጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች የተፈጠሩ መስተጓጎሎችን ለመቅረፍ እና የድንበር ተሻጋሪ የነዳጅ ዝውውርን ለመቆጣጠር አዳዲስ አሠራሮችን እየዘረጋ ነው።

BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

52 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።