Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ቢዝነስ

በኢትዮጵያ እና በኬንያ መካከል የተጀመረው የጠረፍ ንግድ መመሪያ ይፋ ሆነ

BS Bethelhem Solomon Jul 1, 2026 Updated 10h ago 2 ደቂቃ ንባብ 838 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
በኢትዮጵያ እና በኬንያ መካከል የተጀመረው የጠረፍ ንግድ መመሪያ ይፋ ሆነ

የንግድ እንቅስቃሴው በኢትዮጵያ ድንበር በኩል እስከ 50 ኪሎ ሜትር፤ በኬንያ በኩል ደግሞ እስከ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ባሉ አካባቢዎች የተወሰነ ነው።


የንግድ
እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በኢትዮጵያ እና በኬንያ የድንበር አካባቢዎች የሚኖሩ ሕዝቦችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና ሕጋዊ የንግድ ሥርዓትን ለመዘርጋት የሚያስችል አዲስ የጠረፍ ንግድ መመሪያ ይፋ አድርጓል።


ይህ መመሪያ በሁለቱ ሀገራት መካከል ታህሳስ 10 ቀን 2018 . በአዲስ አበባ የተፈረመውን የተቀላጠፈ የጠረፍ ንግድ ማዕቀፍ በተግባር ላይ ለማዋል የወጣ ቁልፍ መመሪያ ነው።

የመመሪያው ዋና ዓላማ በድንበር አካባቢዎች የሚስተዋለውን የኮንትሮባንድ እና ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ በሕጋዊ ሥርዓት በመተካት፤ በአካባቢው ሰላምና ፀጥታን ማስፈን እና የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ይበልጥ ማጠናከር ነው።


በተጨማሪም ከመሀል ሀገር ርቀው የሚገኙ የድንበር አካባቢ ነዋሪዎች መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን በቀላሉ እና በሕጋዊ መንገድ እንዲያገኙ ማድረግ የመመሪያው ዋነኛ ግብ ነው።

በመመሪያው ድንጋጌ መሰረት በጠረፍ ንግድ የሚሳተፍ ማንኛውም ነጋዴ በአንድ ወር ውስጥ የሚያስገባው እና የሚያስወጣው የምርት መጠን ግምት 1,000 የአሜሪካን ዶላር ወይም ተመጣጣኝ የኢትዮጵያ ብር እና የኬንያ ሽልንግ መብለጥ የለበትም።


ነጋዴዎች ይህንን የገንዘብ ገደብ እስካልተላለፉ ድረስ በወር እስከ አራት ጉዞዎችን በማድረግ ምርቶቻቸውን መለዋወጥ እንደሚችሉ ተመላክቷል።


የንግድ እንቅስቃሴው የሚሸፍነው ስፋት በኢትዮጵያ በኩል ከድንበር እስከ 50 ኪሎ ሜትር፤ በኬንያ በኩል ደግሞ እስከ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ባሉ አካባቢዎች የተወሰነ ነው።

Advertisement
Your ad could be here — contact us

ለአንድ ጉዞ በተቀመጠው ገደብ መሰረት እንስሳትን በተመለከተ 2 በላይ ግመል ወይም በሬ እንዲሁም 5 በላይ ፍየል ወይም በግ መገበያየት የተከለከለ ነው።


ለግብርና ምርቶችም ተመሳሳይ ገደቦች የተቀመጡ ሲሆን ለምሳሌ በቆሎን በአንድ ጉዞ ከአንድ ኩንታል በላይ መገበያየት አይቻልም።


በመመሪያው ከተዘረዘሩት 50 የምርት ዓይነቶች መካከል እንስሳት፣ የእንስሳት ውጤቶች፣ የግብርና ምርቶች፣ ቅመማ ቅመም፣ የምግብ ዘይት፣ መጠጦች፣ አልባሳት፣ ጫማ፣ የቆዳ ውጤቶች፣ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች፣ ፍራሽ፣ የስልክ ቀፎዎች እና የጽሕፈት መሣሪያዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ።

ማንኛውም የጠረፍ ንግድ እንቅስቃሴ ሊፈጸም የሚችለው የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የጉምሩክ ሥነ-ሥርዓት አገልግሎት በሚሰጥባቸው የድንበር በሮች ብቻ መሆኑም ሰፍሯል።


የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ወይም ሚኒስቴሩ የሰየማቸው ተቋማት የወጪ ምርቶችን የመሸጫ ዋጋ ግምት የማስላት እና የመቆጣጠር ኃላፊነት የተጣለባቸው ሲሆን ነጋዴዎችም የድንበር ንግድ ፈቃድ በመያዝ በዚህ ሕጋዊ አሠራር ውስጥ እንዲገቡ ጥሪ ቀርቧል።

ይህ አሠራር በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች ከመሀል ሀገር ለማግኘት የሚቸገሩትን መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች በዘላቂነት እንዲያገኙ በማድረግ በሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች መካከል የነበረውን የቆየ ወዳጅነትና የንግድ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል ተብሎ ይጠበቃል።

BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

52 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።