የቤት ኪራይ ዋጋን ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ምክንያት የቤት ኪራይ ቁጥጥር እየተደረገበት ያለው መንገድ አከራይንም ሆነ ተከራይን ለከፍተኛ ጫና መዳረጉን የኢትዮጵያ የሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት አስታወቋል።
አዋጁ ለኪራይ ዋጋ መረጋጋት ቢጠቅምም በአፈጻጸም ሂደት ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ግን የሁለቱንም ወገኖች ህይወት ፈታኝ ማድረጉን የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር አሻግሬ ዘውዱ ገልጸዋል።
በተለይም በገቢዎች መስሪያ ቤት በኩል ለኪራይ ቤቶች የሚጠየቁ የተለያዩ የግብር አይነቶች አከራዮች ዋጋ እንዲጨምሩ እየገፋፋቸው እንደሚገኝ ዶክተር አሻግሬ አያይዘው ገልጸዋል።
በተጨማሪም መንግሥት እንደ “40/60” ባሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ዝቅተኛ የኪራይ ዋጋ ገደብ ማስቀመጡ አከራዮች ገበያው ከሚፈቅደው በላይ እንዲጠይቁ ወይም ግብር ለመሸሽ እንዲገደዱ ማድረጉን ጠቁመው ይህም እንደ ደላላ የሚሰራበት የመንግሥት አሰራር መኖሩን እንደሚያሳይ አስረድተዋል።
በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ቢሮ በቅርቡ ይፋ ባደረገው ጥናት መንግሥት የቤት ኪራይ ዋጋን ለመቆጣጠር ጣልቃ ባይገባ ፤ መካከለኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ለከፍተኛ ችግር ይዳረግ እንደነበር ያመላክታል።
የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ መሪ ተመራማሪ ዶክተር ኖራሁን አንዳርጌ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ከሚያገኘው ገቢ እስከ 80 በመቶ የሚደርሰውን ለቤት ኪራይ እየከፈለ ነው።
ይህም በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካለው 30 በመቶ የቤት ኪራይ ስታንዳርድ ጋር ሲነጻጸር እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ጥናቱ ያሳየ ሲሆን መንግስት ይህን መሰረት አድርጎ በዚህ ዓመት የቤት ኪራይ ላይ መጨመር የሚቻለው 11.5 በመቶ ብቻ ነው ሲል ወስኗል፡፡
የኢትዮጵያ የሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት እስካሁን ለማህበረሰቡ መረጃ የመስጠት እና የመወትወት ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን የገለጹት የቦርድ ሰብሳቢው ዶክተር አሻግሬ በዚህ መንገድ ብቻ ለውጥ ማምጣት ስላልተቻለ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ወደ ህጋዊ ክርክር ለመሸጋገር ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ ድርጅቱ መንግሥት የሚወስዳቸውን እርምጃዎች በፍርድ ቤት እግድ ለማስደረግ እና ጠበቃ በመቅጠር በሸማቹ መብት ላይ ተጽእኖ ለማሳደር ስትራቴጂ እየቀረጸ መሆኑን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ይህ አካሄድ መንግሥት የሚወስዳቸውን እርምጃዎች በህግ እንዲፈተሹ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ቢሮ በበኩሉ በጥናቱ ላይ ተመስርቶ የቤት ኪራይ ዋጋን የሚተመነው መንግሥት እንደሚሆን የገለጸ ሲሆን ይህም የቤት ኪራይ ዋጋን በማረጋጋት በከተማዋ ያለውን የኑሮ ጫና ለመቀነስ ታቅዶ እየተሰራበት መሆኑን አመላክቷል።